መገናኛ ብዙኃን ጥቁር ገበያን ለማስቀረት ከመንግስትና ከህዝብ ጋር ተባብረው ሊሰሩ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

54
አዲስ አበባ ነሐሴ 19/2010 መገናኛ ብዙኃን ጥቁር ገበያን ለማስቀረት ከመንግስትና ከህዝብ ጋር በመተባበር በጋራ መስራት እንደሚገባው ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሳቡ። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ  ከ120 በላይ የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ በዚሁ ወቅት "ጥቁር ገበያ መሻሻል ቢያሳይም በአሁኑ ወቅት እንደገና እያገረሸ መሆኑንና እርሱን ተከትሎም ያሉት ህገ ወጥ ንግዶች እንዳይስፋፉ ምን እየተደረገ ነው?" የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ተነስቶላቸዋል። ጥቁር ገበያን ለመከላከል የኮንትሮባንድ ንግድን ማስቀረት እንደሚገባ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ለመግታትም መገናኛ ብዙሃን ከመንግስትና ከህዝብ ጎን በመሆን ድርጊቱን ለማስቆም "በትኩረት ሊሰራ ይገባል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በተጨማሪም አገሪቷ የኢኮኖሚ እድገት እያሳየች መምጣቷን ጠቁመው፤ አሁንም በውጭ ምንዛሪ ላይ የመጣው ለውጥ በቂ ባለመሆኑ "ለዚህም ህገ ወጥ ንግድንና ጥቁር ገበያን መግታት ተገቢ ነው" ብለዋል። ከኢንጅነር ስመኘው ሞትና ከሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት ጋር በተያያዘ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም  ፖሊስ ምርመራውን እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የተጠናከረ መረጃ ሲኖር ውጤቱ ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል። ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተሾሙበት ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በኋላ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ማብራሪያ ሲሰጡ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም