''ኢትዮጵያ ሰላሟ ተጠብቆ በአፍሪካ ጠንካራ ሀገር ሆና እንድትቀጥል እስራኤል የበኩሏን ድጋፍ ታደርጋለች'' -በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር

99

አዲስ አበባ ታህሳስ 11/2014(ኢዜአ)  ኢትዮጵያ ሰላሟ ተጠብቆ በአፍሪካ ጠንካራ ሀገር ሆና እንድትቀጥል እስራኤል የበኩሏን ድጋፍ እንደምታደርግ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ገለጹ።

አምባሳደሩ ይህን ያሉት በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎች የዓይነት ድጋፍ ባደረጉበት ወቅት ነው።

በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ እና ሶሎሞን ፋውንዴሽን በትብብር 14 ሺህ ኪግ ቁሳቁስ፣ አልባሳት፣ ዊልቸሮችና የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያዎችን ያካተተ ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ተረክበዋል።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ ሁለቱ ሀገራት ረጅም ዘመን ያስቆጠረ የታሪክ፣ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት አላቸው።

ኢትዮጵያ ሰላሟና አንድነቷ ተጠብቆ በአፍሪካ ጠንካራ ሀገር ሆና እንድትቀጥል እስራኤል የበኩሏን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አምባሳደር አለልኝ አክለዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ በአማራና አፋር ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የሁለቱ ሀገራት ህዝብና መንግስት ያላቸው የረጅም ጊዜ ወዳጅነትና ቤተሰባዊነት ዘመን የሚሽረው አይደለም ብለዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ከእስራኤል ህዝብና መንግስት ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩ ሚኒስትሯ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም