በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ቁጠባና የምርት አጠቃቀም ባህልን ማሳደግ ተገቢ ነው

156

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 11/2014(ኢዜአ)  በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የተጎዳው ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ የቁጠባና የምርት አጠቃቀም ባህልን ማሳደግ  ተገቢ መሆኑን  የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት  ሀገሪቱ ለዘርፈ ብዙ ችግሮች እንድትጋለጥና ኢኮኖሚያዊ እድገቷም ወደኋላ እንዲጓተት ምክንያት ሆኗል፡፡

በኢኮኖሚው ላይ የደረሰውን ጫና ለመቋቋም የቁጠባ ባህልን ማሳደግና የምርት አጠቃቀምን ማስተካከል እንደሚገባ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ደገላ አርጋኖ፥ ጦርነቱ ኢኮኖሚው ላይ ያሳደረውን ጫና ለመቋቋም የምርት አጠቃቀምን በማስተካከል ብክነትን መቀነስ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተለይ እንደ ሀገር የዋጋ ወሰን የወጣላቸው እንደ ነዳጅ ያሉ ምርቶችን ከብክነት በፀዳ ሁኔታ መጠቀም ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

አቅርቦታቸው ከገበያ ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ የሆኑ እንደ ስኳርና ዱቄት ያሉ ምርቶች ስርጭት ፍትኃዊ እንዲሆን ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።

ኅብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በስፋት እንዲጠቀም ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ የምርቶች ዋጋ ላይ ግልፅነት መፍጠር እና የከፍተኛ አከፋፋዮች የግብይት ዋጋ የማይዋዥቅ መሆን እንዳለበትም አክለዋል።

መንግስት የሀገር ውስጥ ገቢን የመጨመርና ወጪን የመቀነስ ስልት በመንደፍ ከወትሮ በተለየ መልኩ ተግባራዊ ቢያደርግ ችግሩን ለመቋቋም ሌላው አማራጭ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዶክተር ደገላ ገለጻ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ኪሳራና ብክነታቸውን እንዲቀነሱና ትርፋቸውን እንዲያሳድጉ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ብርሃኑ ጌታቸው በበኩላቸው፥ ኅብረተሰቡ የቅንጦት እቃዎችን ከመግዛት መቆጠብ አለበት ነው ያሉት።

ቁጠባ ችግርን ለማለፍና ነገን የተሻለ ለማድረግ ጠቃሚ በመሆኑ ማንኛውም ግለሰብ ከገቢው 20 በመቶውን ቢቆጥብ ለሀገር እድገት ከፍያለ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት የደረሰውን ሠብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ለመደገፍ የሚያስችል የበጀት ቁጠባ የሚደረግባቸውን የበጀት አርዕስቶች በመለየት እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዚህም መንግስታዊ ተቋማት በጀታቸውን በቁጠባ እንዲጠቀሙ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል።