በአዲስ አበባ ዳያስፖራው የኢትዮጵያ ምርቶችን የሚገዛበት ባዛር ጨምሮ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ተዘጋጅተዋል

86

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 11/2014(ኢዜአ)  በአዲስ አበባ ዳያስፖራው የኢትዮጵያ ምርቶችን የሚገዛበት ባዛር ጨምሮ የተለያዩ መርሃ ግብሮች መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

በመዲናዋ ወደ አገር ቤት የሚገቡ ዳያስፖራዎችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉንም ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ወደ አገር ቤት የሚገቡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው ገልጸዋል።

መጪውን የገና በዓል በኢትዮጵያ ለማሳለፍ ለሚመጡ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ለመቀበል ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።

ከአየር መንገድ ጀምሮ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎች እንግዶችን ተቀብለው እስከ 30 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ ዳያስፖራውን ለመቀበል ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፤ የአስጎብኚ ድርጅቶችና የቱሪስት ታክሲዎች ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

የተለያዩ ባህላዊ ፌስቲቫሎች፣ የኢትዮጵያ ምርቶች የሚሸጡበት ባዛር፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ ሲኒማ እና የግጥም ምሽቶች ለእንግዶቹ መዘጋጀቸውን ገልጸዋል።

ታዋቂ ግለሰቦች ልምድ እና እውቀታቸውን የሚያካፍሉበት መርሃ ግብርም ከዝግጅቱ መካከል መሆኑን የቢሮ ሃላፊዋ ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት በኢትዮጵያዊ መስተንግዶ እንዲቀበል ጥሪ አቅርበዋል።

እንግዶች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የሚፈልጉትን መረጃና አገልገሎት በመስጠት ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በመዲናዋ የሚገኙ ባለሀብቶችና ግለሰቦች ለእንግዳ ማረፊያ ያዘጋጇቸውን ቤቶች በየክፍለ ከተማው ባሉ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤቶች በመሄድ ከዛሬ ጀምሮ ማስመዝገብ እንዳለባቸውም ነው ዶክተር ሂሩት የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት እንዲመጡ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ እስካሁን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለመምጣት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ባሰለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ላይ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

‘የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የአገር ቤት ጉዞ ጥሪ’ ዓላማ የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት፣ በውጭ መገናኛ ብዙኃን ስለ ኢትዮጵያ የሚሰራጨውን ሐሰተኛ መረጃ በመቀልበስ እውነቱን ለዓለም ማሳወቅ እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻዎችና የልማት ቦታዎች ማስተዋወቅ እንደሆነም መገለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም