የሰላም ሚኒስቴር በፌዴራል ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ የግንዛቤ ክፍተቶችን ለማረም እየሰራ ነው

180

አዳማ ታህሳስ 11/2013 ..(ኢዜአ) በህብረ ብሔራዊ ፌዴራል ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ የፅንሰ ሃሳብ አረዳድና የግንዛቤ ክፍተቶችን ለማረም እየሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የግንዛቤ ክፍተቶችን በጥናትና ምርምር ለመቅረፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ  ከተለያዩ ተቋማትና ከዩኒቨርሲቲዎች ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ እየመከረ ነው።

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አማካሪ አቶ ካይዳኪ ገዛኽኝ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ባለብዙ ማንነቶችና ልዩነቶች ባለቤት በመሆኗ ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓት “ብዝሃነትና ልዩነቶችን በእኩልነት ለማስተናገድ የተሻለ አማራጭ ነው” ብለዋል።

በህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓቱ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የተሰሩ ስራዎች ቢኖሩም ክፍተቱ ጎልቶ እንደሚታይ ተናግረዋል ።

“በፌዴራል ስርዓቱ ላይ ከግንዛቤና አረዳድ ጀምሮ ሰፊ ክፍቶች ነበሩ” ያሉት አማካሪው የዛሬው መድረክም የሚስተዋሉ የፅንሰ ሃሳብ አረዳድና የግንዛቤ ክፍተቶችን ለማረም የሚያስችሉ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

“የህብረ ብሔራዊ ፌዴራል ስርዓቱ ለሀገሪቱ አስፈላጊ መሆኑን አብዛኛው ምሁራንና ልሂቃንን ጨምሮ በማህበረሰቡ ዘንድ መግባባት አለ” ያሉት አቶ ካይዳኪ እንዴት መተግበር አለበት በሚለው ላይ ክፍተቶቹን ለመሙላት ውይይት ማስፈለጉን አስታውቀዋል።

የህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማእከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሃይለየሱስ ታዬ በመድረኩ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ  “የፌዴራልዝም መነሻ እሳቤ በአብሮነትና በጋራ በመቻቻል መኖር ነው” ሲሉ አመልክተዋል።

“ይሁንና ባለፉት ዓመታት ስርአቱ ከዚህ በተቃርኖ በመተግበሩ አገሪቱ  ወደ ግጭቶች ገብታለች” ሲሉ አክለዋል።

“ስርአቱ ሚዛኑን ጠብቆ በትክክል ከተተገበረ አገሪቱ ያላትን ብዝሃነት አስጠብቆ በአብሮነት መኖር ያስችላል” ያሉት ዶክተር ሃይለየሱስ   በስርአቱ የጽንሰ ሀሳቦች አረዳድና ሚዛኑን ጠብቆ ያለመተግበር ችግሮች ሊቀረፉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

“በተለይም በፌዴራል ስርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን የፅንሰ ሃሳብ አረዳድና የግንዛቤ ክፍተቶችን በተገቢው መንገድ ማከም እንዲሁም ማንነትና ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ፤ ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና እድገታችን የላቀ ሚና ይኖረዋልም” ሲሉ ዶክተር ሃይለየሱስ አስታውቀዋል።

የውይይት መድረኩ ለሁለት ቀን እንደሚቆይ ከመርሀ ግብሩ ለማወቅ ተችሏል።