በቀጣይ አምስት ዓመታት የእርሻ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ቡና አምራች አርሶ አደሮችን ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

179

ዲላ ፣ ታህሳስ 11/2014 (ኢዜአ) በአነስተኛ ማሳ ቡና የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም በማደራጀት ምርታማነትና ጥራትን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

የኩታ ገጠም የቡና አመራረት ቴክኖሎጂ ሀገር አቀፍ የመስክ ጉብኝት በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ ተካሂዷል።


በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት መሪ ተመራማሪ ዶክተር ተስፋዬ ሽብሩ በጉብኝቱ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ቁጥር ከ5 በመቶ አይበልጥም።


የአርሶ አደሩ ቴክኖሎጂን በስፋት አለመጠቀም በሄክታር የሚገኘውን ምርት አነስተኛ ከማድረጉ ባለፈ የሀገሪቱ ቡና ዓለም አቀፍ የምርት ጥራት ደረጃው እንዲያሽቆለቁል ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ በአነስተኛ ማሳ ቡና የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም በማደራጀት ምርታማነትና ጥራትን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

“አርሶ አደሩ በምርምር የተለየ መነሻ ዘር ከማቅረብ አንስቶ እስከ ድህረ ምርት ቴክኖሎጂና የተሻሻሉ የአሰራር ስርዓቶችን እንዲላመድ ጥረት እየተደረገ ነው” ብለዋል።

“በቀጣይ አምስት ዓመታት በተበጣጠሰ መሬት ቡና የሚያመርተውን ሰፊውን አርሶ አደር በኩታ ገጠም በማደራጀት ዝቅተኛ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል ወደ 50 በመቶ ለማሳደግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው” ሲሉም አመልክተዋል።

በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ የተጀመረውን በኩታ ገጠም ቡና የማልማት ተሞክሮን ለማስፋት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ማሳቸውን ያስጎበኙትና ተሞክሯቸውን ያካፈሉት አርሶ አደር ወርቁ ወሬራ እንዳሉት የአካባቢው ሰባት አርሶ አደሮች ተደራጅተው ከ15 ሄክታር በላይ በሆነ ኩታ ገጠም ማሳቸው ላይ በጋራ ቡና እያለሙ ነው።


ከዚህ ቀደም ያረጀ የቡና ዛፍ በመጎንደል ከሚደረግ እድሳት በኋላ ተክሉ ለሁለት ዓመት ያክል ምርት ባለመስጠቱ አርሶ አደሩ እራሱን የሚደጉምበት አማራጭ በማጣት ያረጀ የቡና ዛፎ ይዞ ለመቆየት ይገደድ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከዚህ ቀደም ከሚተክሉት ዝርያ የምስራች ምርት ለማግኘት ሶስት ዓመት ይጠብቁ እንደነበር የገለጹት አርሶ አደሩ፥ አዲስ የተከሉት የቡና ዝርያ በ1 ዓመት ከ6 ወር ጊዜ የመጀመሪያ የምስራች ምርት መስጠቱን በአጭር ጊዜ የተሻለ ምርት ለማግኘት ያስችላል ብለዋል።

የገበያ አማራጮችን ከማስፋት ባለፈ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ለችግር እንዳይዳረጉ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ክልል ቡና፤ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ዘርፉ ናቸው።

ቡና አምራች አርሶ አደሩ በተለይ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ደባል ሰብሎችን እንዲያመርት ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ባረጀ የቡና ዛፍ እድሳት ወቅት ግብዓትና የሙያ ድጋፍ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።


በቡና ልማት ጉብኝቱ በሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የግብርና ምርምር ተቋማት ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች የደቡብ፣ ሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች የቡና ዘርፍ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የጌዴኦ ዞን ቡና አምራች አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።