በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎችና የግብርና ምርምር ማእከላት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተሳተፉ ነው

185

ጎንደር ፣ ታህሳስ 11/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሰባት ዩኒቨርሲቲዎችና የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በቀጥታ ከመሳተፍ ጎን ለጎን የእውቀትና ቴክኖሎጂ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ ዶክተር ሃይለማርያም ከፍያለው ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር የሚገኙ ምርምር ማዕከላት በ5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በምርምርና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመስኖ ስንዴ ልማት ጀምረዋል፡፡

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተሳተፉ ያሉት ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ እንጅባራ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃንና ደባርቅ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም የባህርዳር፣ የጎንደርና የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲዎች እያንዳንዳቸው ከ500 ሄክታር በላይ መሬት ላይ በዘመናዊ መንገድ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን እያካሄዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና በሥሩ የሚገኙ ምርምር ማእከላትን በማስተባበር በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በሞዴልነት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መጀመሩን ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱ በስራቸው በሚገኙ የግብርና ምሁራንና ተመራማሪዎች አማካኝነት በአካባቢው በስንዴ ልማት ለተሰማሩ አርሶ አደሮች በግብዓት፣በሙያና በቴክኖሎጂ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የስንዴ ልማቱ አሸባሪው ህወሓት በክልሉ በሰብል ላይ ያደረሰውን ውድመት ማካካስ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ከውጪ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካትን አላማ አድርጎ የሚካሄድ መሆኑን  ዶክተር ሃይለማርያም አስታውቀዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በክልሉ እየተካሄደ ያለውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማገዝ 700 ሄክታር መሬት መረከቡን ተናግረዋል፡፡

"ዘመናዊ አሰራሮችንና ቴክሎጂዎችን የተከተለ የስንዴ ልማት በማካሄድ የክልሉን እቅድ ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ  ለስንዴ አልሚ አርሶ አደሮች የሙያ ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለልማቱ የሚያስፈልገውን የዘር አቅርቦት ለመደገፍ በ320 ሄክታር መሬት ላይ የምርጥ ዘር ብዜት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል ሃላፊ አቶ አስፋው አዛናው ናቸው፡፡

ማእከሉ ድርቅንና ተባይን እንዲሁም የዝናብ እጥረትን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ የስንዴ ዝርያዎችን በማእከላዊ፣ በምእራብና በሰሜን ጎንደር ዞኖች የማላመድና የማስተዋወቅ ሥራ እያካሄደ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 80 ሺ ሄክታር መሬት በማልማት 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም