ኢትዮጵያ በአሸባሪው ላይ እየወሰደች ያለው እርምጃ የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት የሚቀለብስ ነው

80

ባህር ዳር ታህሳስ 11/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ አሸባሪው ህወሃት ላይ እየወሰደች ያለው እርምጃ የአንዳንድ ምእራባውያንን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ለመቀልበስ እንደሚያስችል ሴት ጋዜጠኞች ተናገሩ።

ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በማዋል በግንባር እየተዋደቁ ለሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች ድጋፍ እያደረጉ ያሉ ሴት ጋዜጠኞች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሀገርን ለማፍረስ በተነሳው አሸባሪው ህውሃት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ የኢትዮጵያን ጠንካራ አቋም የሚያስመሰክር ነው።

ይህም የአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት  ፍርደ  ገምድል ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ለመቀልበስ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ጋዜጠኛ ስመኝ ግዛው፤ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን በራሷ አቅም የማስከበር ብቃት እንዳላት በተግባር እያሳየች መሆኗን ገልጻ ወራሪውንና አሸባሪውን ሃይል ስርዓት ለማሲያዝ ኢትዮጵያ እየወሰደች ያለው እርምጃ የውጭ ጫና እንደሚቀንሰው አመልክታለች።

"ዋናው ነገር አሁን የተገኘውን ውጤት አስጠብቆ በማስቀጠል ቡድኑ ዳግም የጥፋት እጁን እንዳያነሳ ማድረግ ዓይነተኛ መፍትሄ ነው" በማለትም ገልፃለች።

የምዕራባውያኑን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ለመከላከል እና የአሸባሪው ቡድን የጥፋት ተልዕኮን ለማምከን እየገሰገሱ ለሚገኙት የፀጥታ ሃይሎች መላ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፋ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያለችው ደግሞ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዝን( ኢሳት) ጋዜጠኛ የምስራች አጥናፉ ናት።

ኢትዮጵያ አሁን ሁለተኛውን የአድዋ ድል ለመድገም ከጫፍ ደርሳለች ያለችው ጋዜጠኛዋ ፤ ውጤቱ በዚሁ ከቀጠለ የአንዳንድ ምዕራባውያንን ጫና መቀልበስ እንደሚያስችል ተናግራለች።

አሸባሪውን የህወሃት ቡድንን የጥፋት ተልዕኮ ለማክሸፍ ኢትዮጵያ እየወሰደች ያለው እርምጃ ያልተገባ የውጭ ጫና ለመቀነስ የሚያስችል በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያለችው ደግሞ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ጋዜጠኛ አዜብ ታምሩ ናት።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሉአላዊነት የማስከበር ስራ አጠናክራ የውጭውንም ሆነ ውስጡን  ጫና በአሸናፊነት እንድትወጣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ  ድጋፉን መቀጠል  እንዳለበት አመልክታለች።

በውጭና ውስጥ ያለ ኢትዮጵያዊ የሀገሩን ሉዓላዊነት ላለማስደፈር ሆ ብሎ እንደተነሳ ጠቅሳ "ትብብሩ አሸባሪው የኢትዮጵያ ስጋት እስከ ማይሆንበት ድረስ መጠናከር አለበት" ስትል ተናግራለች።

አምስት ሴት ጋዜጠኞች ማህበራዊ የትስስር ገፆችን   በመጠቀም ያሰባሰቡትን 700 ሺህ ብር የሚገመት ስንቅ ለጥምር ጸጥታ ኃይሉ ድጋፍ  ማድረጋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም