አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ፋይናንስ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል

375

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11/2014(ኢዜአ) አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ፋይናንስ በማድረግ የፈጠራ ባለቤቶቹን ወደ ኢንቨስትመንት ለማስገባት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ገለጸ።

የአገሪቱን የኢንቨስትመንት ፍላጎትና የባንኩን ተልዕኮ ያጣጣመ የቢዝነስ ሞዴል መዘጋጀቱም ባንኩ ጠቁሟል።

የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባንኩ በተያዘው ዓመት 19 ቢሊዮን ብር ብድር ለማቅረብ እየሰራ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም የተለያዩ የብድር አይነቶችን ሲያቀርብ መቆየቱን ገልጸው፤ አሁን ደግሞ አዲስ የፋይናንስ አቅርቦት ለመጀመር ተዘጋጅቷል ብለዋል።  

ይህም አዳዲስ የፈጠራ ኃሳቦችን ፋይናንስ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንን ሥራ የሚያካሂድ ራሱን የቻለ ክፍል እንደተቋቋመለት ጠቁመዋል።

በዚህም መሰረት የባለቤትነት ማረጋገጫ (ፓተንት) ያገኙ የፈጠራ ባለቤቶችን በገንዘብ ለመደገፍ ባንኩ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።  

ይህም ወጣቶች ወደ ኢንቨስትመንት ሥራ በቀላሉ እንዲገቡ ትልቅ እድል እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ፍላጎትና የባንኩን ተልዕኮ ያጣጣመ የቢዝነስ ሞዴል በማዘጋጀት ዘርፍ ተኮር አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷልም ብለዋል።

ባንኩ በየዘርፉ ራሱን የቻለ የሥራ ክፍል እንዲቋቋም እንደሚያስችለው ጠቁመው፤ ይህም የባንኩን አሰራር በማዘመንና ቀልጣፋ በማድረግ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።   

ጎን ለጎንም በየክልሉ ያለውን አቅምና የገበያ ሁኔታ እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ ሃሳቦች የሚሰጥ የልማት ጥናት ዘርፍ መቋቋሙንም ተናግረዋል።

ባንኩ የሚገጥመውን የተበላሸ ብድርንና ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ተደራሽነቱን በሁሉም ቦታዎች ለማስፋት አሁን ካለበት ከ78 ቅርንጫፍ ወደ 110 ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ባንኩ ቀልጣፋና ግልፅነት ያለው አሰራርን በመከተል ደንበኞቹን በማገልገሉም ባለፈው ዓመት 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ማትረፉን ገልፀዋል።