“ከስደት መልስ የቤተሰቦቼን ናፍቆት ሳልወጣ የአሸባሪው ህወሓት ጥይት ከቤት አስቀምጦኛል”

211

ታህሳስ 11 2014 (ኢዜአ) ወጣት እመቤት ደሳለኝ ትባላለች ፤ ከዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ከቤተሰቦቿ ጋር ብትቀላቀልም 1 ወር እንኳን ሳይሞላት በአሸባሪው ህወሓት ጥይት ቆስላለች።

ውልደትና እድገቷ ውጫሌ ከተማ የሆነው የ24 ዓመቷ ወጣት እመቤት ‘ሕይወቴን እቀይራለሁ፤ ቤተሰቦቼንም መርዳት ያስችለኛል’ በማለት ወደ ዱባይ በማቅናት ለአምስት ዓመታት ሰርታለች።

የዱባይ ቆይታዋን አጠናቃ ወደ አገሯ በመመለስ በትውልድ መንደሯ ውጫሌ ከተማ ቤተሰቦቿ ጋር በማረፍ ናፍቆቷን እየተወጣች መቆየት የቻለችው ግን ለ27 ቀናት ብቻ ነው።

ባሳለፍነው መስከረም የመጨረሻው ሳምንት በአንዱ ቀን አመሻሹ ላይ የህወሓት የሽብር ቡድን ወራሪዎች ወደ እነ እመቤት ቤት በመምጣት ከአካባቢው የሸሹ ጎረቤቶቻቸውን በር እንዲከፍቱ አስገደዷቸው።

እነ እመቤት ቤት ከ12 ዓመት ወንድ ልጅ በቀር አዋቂ ወንድ ስላልነበረ የቤቱን ቁልፍ መስበር የሚችል አልተገኘም።

ወትሮም ሰው ለመግደል ሰበብ የሚፈልጉት የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች የመሳሪያቸውን አፈሙዝ ወደ ቤቱ በማዞር ይተኩሳሉ፤ በተኩሱ እመቤት ደሳለኝ ጭኗ ላይ በመመታቷ አጥንቷ ሲሰበር ታላቅ እህቷ ፀሐይ ደሳለኝም በተመሳሳይ ተመትታ ጉዳት አጋጥሟታል።

የቤተሰቦቿን ናፍቆት እንኳ ያልተወጣችው ወጣት እመቤት በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች እኩይ ተግባር ምኞቷ እንደጉም በኖ የመከራ ጊዜ መግፋት ጀምራለች።

የሽብር ቡድኑ ወራሪዎች የሰዎችን እንቅስቃሴ በመገደብ፣ የሕክምና ተቋማትን በማውደምና መድሃኒቶችን በመዝረፍ የወጣቷን በሕክምና ክትትል የመዳን ተስፋ አጨልመውትም ቆይተዋል።

የጥቃቱ ሰለባ የሆነችው ታላቅ እህቷ ወይዘሮ ፀሐይ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ውጫሌ በቆዩበት ጊዜ የደረሰባቸውን ሰቆቃ የምትገልጸው በሲቃ ነው።

“የአጎታችን አራት የቤተሰብ አባላት በአንዲት ቅጽበት በከባድ መሳሪያ ተገደሉ፣ መውጣት መግባት ስለተከለከልን አንድ አካባቢ ሆነን አጎታችን ብቻውን አራት አስክሬን እንዲቀብር ተደረገ” ብላለች።

ያሳለፍነው ጊዜ እጅግ መራር ቢሆንም የሞቱት ሞተው እኛ በሕይወት በመቆየታችን ተመስገን እንላለን ስትል ነው የገለጸችው።