የውስጥና የውጭ ጫናዎችን በመቋቋም የገቢና ወጪ ንግዱን የማሳለጥ አቅምና ዝግጁነት አለ

182

ታህሳስ 11 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የውስጥና የውጭ ጫናዎችን ተቋቁሞ የገቢና ወጪ ንግዱን የማሳለጥ አቅምና ዝግጁነት እንዳለው አስታወቀ።

ከኮቪድ 19 ወረርሺኝ በኋላ ዓለም ዓቀፍ የንግድ ስርዓቱ የተለያዩ ፈተናዎች ተጋርጠውበት አገራት ሲፈተኑ ቆይተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የባዶ ኮንቴይነር እጥረት ደግሞ በተለይም የወጪና ገቢ ንግዱን ጎድቶታል።

ይህም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲናጥ የቆየውን የደሃ አገራት ኢኮኖሚ ያልተገባ የዋጋ ግሽበት አስከትሎበት አልፏል።

ኢትዮጵያም የዚሁ ችግር ሰለባ እንደነበረች የተናገሩት የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሮባ መገርሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካጋጠሙ ችግርች በተጨማሪ ኢትዮጵያ የአሸባሪው ሕወሓት የጥፋት እንቅስቃሴም ሌላ ችግር ሆኖባታል ብለዋል።

ሆኖም ድርጅቱ ከዚህ በፊት መልካም ስም የገነባ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ደንበኞችን በሚገባ አሳምኖ የወጪና ገቢ ንግዱ ያለምንም ብልሽት እንዲቀላጠፍ አድርጓል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በሚመቻትና የተሻለ ውጤት በምትለው ኮሪደር የንግድ ሎጂስቲክሱን እያሳለጠች እንደሆነም ጠቁመው ”በየትኛውም ኮሪደር የኢትዮጵያን ጭነት ማስተናገድ የሚያስችል ዝግጁነት አለ” ሲሉ አረጋግጠዋል።

አክለውም የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በፈተና ውስጥ ማለፍ የሚያስችል በቂ አቅምና ዝግጅት አለው ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው።