በዝዋይ ኃይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ 21 ድርጅቶች ወደ ስራ ገብተዋል

259

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11/ 2014 (ኢዜአ) በዝዋይ ኃይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ 21 ድርጅቶች ወደ ስራ ገብተዋል።

በሁለት ሳምንት ብቻ ከ9 ነጥብ 5 ሄክታር በላይ የነበረን አረም ማስወገድ መቻሉም ታውቋል።

በኃይቁ ላይ አረሙ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ተለይተው ድርጅቶቹ አረሙን የሚነቅሉባቸውን ስፍራዎች ተረክበዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ኃይቆች ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት ሕዝባዊ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ኃብታሙ ኢተፋ ተናግረዋል።

በዝዋይ ኃይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተደረገ ዘመቻ ከ9 ነጥብ 5 ሄክታር በላይ የሸፈነ አረም ማስወገድ መቻሉንም ገልጸዋል።

የተለያዩ ድርጅቶች አረሙን ለማስወገድ ቦታ ተረክበው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመው ይህም አረሙን ለማጥፋት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በኃይቁ ላይ በዚህ ዓመት 388 ሄክታር የሚሸፍን አካባቢን ከአረሙ ለማፅዳት ዕቅድ መያዙን የተናገሩት ሚኒስትሩ የተጀመረው ሕዝባዊ ንቅናቄ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር ሚሊዮን በቀለ በበኩላቸው በክልሉ በተለይ በምስራቅ ሸዋ በሚገኙ ኃይቆች ላይ የእምቦጭ አረም እየተስፋፋ በመሆኑ ለማጥፋት ቀጣይነት ባለው መልኩ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አረሙን ለማስወገድ ወደ ስራ የገቡት ተቋማትም ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የዝዋይ ኃይቅ በዓሳ ምርቱ እንዲሁም በማራኪ የተፈጥሮ ሐብቶቹ ይታወቃል።

የእምቦጭ አረም የጣና እና ዝዋይ ኃይቆችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለተፈጥሮ ኃብት የሕልውና አደጋ እየሆነ መጥቷል።