በውጫሌ ከተማ አራት የቤተሰብ አባላት በሽብር ቡድኑ በመድፍ ተገድለዋል

305

ታህሳስ 11/2014 (ኢዜአ)በውጫሌ ከተማ አራት የቤተሰብ አባላት በአሸባሪው ህወሓት በተተኮሰ መድፍ ተገድለዋል።

‘ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እወርዳለሁ’ በማለት የጥፋት እጁን የዘረጋው አሸባሪው ህወሓት በንጹሃን ዜጎች ላይ ያልፈጸመው አይነት ሰቆቃ የለም።

የሽብር ቡድኑ የመከላከያ ሠራዊትና የጸጥታ ኃይሎችን ምት መቋቋም ሲሳነው ንጹሃንን መግደልና ሀብትና ንብረት ማውደምን መገለጫው አድርጎታል።

የጀመረው ጦርነት ራሱን ሲበላው ሽንፈቱን የመኖሪያ ቤቶችን በከባድ መሳሪያ በመደብደብ ንጹሃንን በመግደል የጭካኔን ጥግ አሳይቷል፡፡

የውጫሌ ከተማ ነዋሪው ሃምሳ አለቃ ፈንታዬ ሞላ ከሽብር ቡድኑ ጥቃት ሰለባዎች አንደኛው ናቸው።

የሽብር ቡድኑ ወደ ውጫሌ ከተማ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ አራት የቤተሰባቸውን አባላት ሲገድል ሌሎች አራቱን ደግሞ ከባድ የመቁሰል አደጋ እንዳደረሰባቸው ገልጸዋል።

ሃምሳ አለቃ ፈንታዬ በሽብር ቡድኑ የከባድ መሣሪያ ድብደባ ባለቤታቸውን፣ የልጃቸውን ሚስት እንዲሁም የወንድማቸውን ልጆች አጥተዋል፤ ሁለት መኖሪያና አንድ ኩሽና ቤት ሙሉ በሙሉ ሲወድምባቸው ስድስት በጎቻቸውም መሞታቸውን ተናግረዋል።

በወቅቱ የአካባቢው ሰው በስጋት ምክንያት መውጣት ባለመቻሉ አራት አስክሬን ይዘው ማደራቸውንና ሲነጋም ራሳቸው እየዞሩ ቤተሰቦቼ አልቀዋል አቃብሩኝ ብለው ተጣርተው መቅበራቸውን ነው የገለጹት።

የሟች ቤተሰብ የሆኑት ወይዘሮ አረጋሽ ሀይሌ ድብደባው በተፈጸመበት ቅጽበት ከቦታው ቢደርሱም ሶስቱ ሕይወታቸው አልፎ እንዳገኟቸው፤ አራተኛዋም ክንዳቸው ላይ አቅፈዋት ሕይወቷ ማለፉን ገልጸዋል።

ከሟቾቹ መካከል የአራተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረው ወጣት ቤተሰቦቹን ቦታ ለመቀየር ወደቤት ሲገባ ከባድ መሳሪያው በመተኮሱ እዚያው አብሯቸው መሞቱን ተናግረዋል።

እናትና ባለቤቱን በአንድ ጊዜ የተነጠቀው የሃምሳ አለቃ ፈንታዬ ልጅ አቶ ገበየሁ ፈንታዬም በወቅቱ አራት የቤተሰቦቻችንን አባላት አጥተን “ማልቀስ አትችሉም” ተብለን ተከልክለናል ነው ያለው።

ከአንድ ቤተሰብ አራቱ ሞተው፣ አራቱ ቆስለው፣ ስድስት በጎች ተገድለው፣ ሶስት ቤት ሙሉ በሙሉ ወድሞ ሀዘንን አለመግለጽ “እጅግ ከባድ” ነበር ሲል ነው የገለጸው።