በአሸባሪው ህወሓት የተጎዱ ወገኖች እስኪቋቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን

204

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 11/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ወደ ቀድሞ ህይወታቸው እስኪመለሱ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሀዋሳ ከተማ ሴቶች አስታወቁ ፡፡

አሸባሪው ህወሓት በሴቶችና ህፃናት ላይ እየፈፀመ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ጥቃትና የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራትና መገናኛ ብዙሃን ጣልቃ ገብነትን ለማውገዝ በተካሄደ ሰልፍ ላይ የተሳተፉ የሀዋሳ ከተማ ሴቶች ለኢዜአ እንደገለጹት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀደመ ህይወታቸው እስኪመለሱ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው ለማስቀጠል ተዘጋጅተዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ሠላም ሉሉ አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በንፁሀን ዜጎችና በተቋማት ላይ ያደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ዘግናኝ መሆኑን ገልጸው “በተለይ በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈጸመው ጥቃት  ከጭካኔም በላይ ነው” ብለዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ምግብ፣ አልባሳት፣ መጠለያና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎታቸው ሊሟላላቸውና ከትምህርታቸው የተስተጓሉ ሕፃናት የትምህርት አገልግሎት ሊያገኙ እንደሚገባ ተናግረዋል።

”ለወገኖቹ የሚውል ድጋፍ እስካሁን በተለያዩ ማህበራዊ አደረጃጀቶች በኩል ስናደርግ ቆይተናል” ያሉት ወይዘሮ ሠላም ወደ  ቀደመው ሠላማዊ ህይወታቸው እስኪመለሱ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች ወጣቶችን በመግደል አዛውንቶችን ያለጧሪ ማስቀረታቸውንና መነኩሴዎችን ጭምር በመድፈር የአረመኔነታቸውን ጥግ ማሳየታቸውን የተናገሩት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ዘይነባ ኡመር ናቸው።

“የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ የምናደርገውን ድጋፍ አናቋርጥም” ያሉት ወይዘሮ ዘይነባ፤ በኢትዮጵያዊነት እሴት ሁሉም ያለውን በማካፈል መልሶ ማቋቋም የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በቋሚነት መደገፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ወይዘሮ ወጋየሁ ሻንቆ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በንፁሐን ወገኖች ላይ የፈፀመው የግፍ ድርጊት ፍፁም ከሰውኛ ባህሪ የራቀ  መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን ወንጀል ተመልክቶ በዝምታ ማለፍና ከማውገዝ መቆጠብ በራሱ ሰብዓዊነት የጎደለው እንደሆነ አመልክተዋል።

ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በመደገፍ  የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

እያደረጉ ያሉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ እስከመጨረሻው አጠናክረው እንደሚቀጥሉ  ጠቁመዋል።

በቅርቡ በሀዋሳ ከተማ ከሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉ የሚታወቅ ነው።