ኢዜአ እና ኢቢሲ ትብብራቸውን ይበልጥ በማጠናከር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

103

ታሀሳስ 11/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ትብብራቸውን ይበልጥ በማጠናከር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረሙ።

የተደረሰው ስምምነት ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን የሰው ሃይል፣ መረጃ፣ ንብረት፣ ልምድና ሌሎች ሃብቶቻቸውን በትብብር በመጠቀም ለአገር ግንባታ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር የሚያግዛቸው መሆኑ ታውቋል።

የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ፤ ሁለቱ ተቋማት በትብብር የመስራት ሂደት የቆየ ልምዳቸውን አስታውሰው የአሁኑ ስምምነትም ይበልጥ በትብብር እንዲሰሩ ያስችላቸዋል ብለዋል።

የተደረገው ስምምነት የሰውሃይልን፣ ንብረትን፣ መረጃን በትብብር በመጠቀም ለሁለቱ ተቋማት ተልዕኮ አፈጻጸምና ለአገር ግንባታ አስተጽኦ ለማበርከት የሚያግዛቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

በመግባቢያ ስምምነቱ የተካተቱ ጉዳዮችን በአግባቡ በመተግበር ተቋማቱ ለኢትዮጵያ እድገትና ልማት አስተዋጽኦ እንድሚያደርጉም ገልጸዋል።

በመገናኛ ብዙሃን መካከል ያለው የፉክክር መንፈስ እንደተጠበቀ ሆኖ በትብብር የመስራት ልምዱ ለሌሎችም ተሞክሮ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ሁለቱ ተቋማት በትብብር ለመስራት ያደረጉት ስምምነት ህዝብ ለማገልገል የያዙትን ተልእኮ ለማሳካት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ኢዜአ ከኢቢሲ ጋር ባደረገው ስምምነት ይበልጥ ተባብሮ በመስራት ኢትዮጵያ የያዘችውን እቅድ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት በሚዲያ ዘርፍ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ተቋማት ያዳበሩትን ልምድና አቅም በጋራ በመጠቀም የተቋማትን ፍላጎት ከማሳካት ባለፈ እንደ አገር በመገናኛ ብዙሃን ትብብርን ለማስፋት አዲስ ተሞክሮ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚው ጠቅሰዋል። 

የትብብር ስምምነቱን የፈረሙት የየተቋማቱ ዋና ስራ አስፈፃሚዎች ኢዜአ እና ኢቢሲ በቀጣይም በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ኢዜአ ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ የዜና አገልግሎት ተግባር በማከናወን ላይ የሚገኝ ብቸኛው ተቋም ሲሆን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአሁኑ ኢቢሲ ደግሞ በ1957 ዓ.ም ነው የተመሰረተው፡፡

በስምምነቱ መሰረት ሁለቱ የሚዲያ ተቋማት ያላቸውን የሰው ሃይል፣የመረጃ፤ንብረትና ሌሎችን በትብብር በመጠቀም ለአገር አስተዋጽኦ ማድረግ የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም