በጉጂ ዞን በዝናብ እጥረት የጠፋውን ምርት በመስኖ ለማካካስ እየተሰራ ነው

165

ነገሌ፣ ታህሳስ 11/2014/ኢዜአ/ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በዝናብ እጥረት የጠፋውን ምርት በዘንድሮው የበጋ ወራት በመስኖ ለማካካስ ከታቀደው መሬት ውስጥ እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ 72 በመቶ ያህሉ በተለያየ አትክልት መልማቱን የዞኑ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በዞኑ በዝናብ እጥረት የጠፋውን ምርት በዘንድሮው የበጋ ወራት በባህላዊ መስኖ ለማካካስ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ መንግስቱ ሂርባዬ እንዳሉት  በዘንድሮው የበጋ ወቅት በመስና ለማልማት ከታቀደው ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ እስካሁን 13 ሺህ 600 ሄክታር ያህሉ በተለያየ አትክልትና ስራስር  ለምቷል፡፡

በመስኖልማቱ  42 ሺህ 373 አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ከመካከላቸው 6ሺህ 300 ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለሙያው እንዳሉት የመስኖ ልማቱ ተሳታፊዎች ምርታማነትን አሳድገው ውጤታማ እንዲሆኑ ከ1 ሺህ 950 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ የተለያየ የአትክልት ምርጥ ዘርና የስራስር ዝርያ ቀርቦ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡

በዞኑ በዘንድሮው የበጋ ወራት በመስኖ ከሚለማው ከዚሁ መሬት  ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን  

ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በግርጃ ወረዳ ከሀረንፋማ ዴቢሳ ቀበሌ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ታከለ ሀለኬ በሰጡት በመኸር ግብርና ያለሙት ሰብል በአጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት ለውጤት ሳይበቃ ቀርቷል፡፡

በመኸር እርሻው ያጡትን ምርት በበጋ ወራት በመስኖ በማልማት ለማካካስ በግማሽ ሄክታር የእርሻ ማሳቸውን በቲማቲምና ቃሪያ   እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ በመስኖ እያለሙት ካለው የእርሻ ማሳ 60 ኩንታል የቲማቲም እና ቃሪያ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ ሲሆን ፀረ -ተባይ ኬሚካል  እንዲቀርብላቸው ጠይቀው እየጠበቁ  መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በወረዳው ሌላው  ቀበሌ  01 ተሳታፊ አቶ ይሳቅ ሰጠኝ እንዳሉት አንድ  ሄክታር የእርሻ ማሳቸውን በቃሪያ፣ ድንች፣ ጎመንና ቲማቲም  በመስኖ አልምተዋል፡፡

በመስኖ ያለሙት አትክልት በጥሩ ሁኔታ ላይ ስለሚገኝ በዝናብ እጥረት ሳቢያ ያጡትን  የሰብል ምርት እንደሚያካክስላቸው ተስፋ  አድርገዋል፡፡

በጉጂ ዞን ባለፈው ዓመት የበጋ ወራት  16 ሺህ ሄክታር መሬት በባህላዊ መስኖ ለምቶ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን  ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከጽህፈት

 ቤቱ  የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡