በበጀት ዓመቱ ለሚከናወኑ 17 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች 9 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ተመድቦ እየተሰራ ነው

72

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11/2014 (ኢዜአ ) በ2014 በጀት ዓመት ለሚከናወኑ 17 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች 9 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

በኢትዮጵያ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቋቋምና በምግብ ራስን ለመቻል የመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ ከሕልውና ዘመቻው ጎን ለጎን ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ብሎም ቀጣይ ሊያስከትል የሚችለውን ጫና የሚቋቋም ምጣኔ ሀብት ለመገንባት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከፍተኛ ማህበራዊ ጉዳት ማድረሱን ጠቅሰው አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቋቋም እና የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ በግብርናው ዘርፍ በስፋት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በእርዳታና በድጋፍ ስም የሚመጡ መልከ ብዙ ፖለቲካዊ ጫናዎችን መቋቋም የሚቻልው በምግብ ራስን ሲቻል በመሆኑ መንግስት በመስኖ ልማት የግብርና ዘርፍ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከ5 እስከ 10 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመስኖ መልማት የሚችል ዕምቅ አቅም ቢኖራትም እስካሁን ማልማት የተቻለው 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ሰፋፊና መካከለኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ በተለይም በመስኖ ስንዴ ማምረት ላይ በመንግስት ልዩ ድጋፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2014 በጀት ዓመት 17 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ገቢራዊ ለማድረግ 9 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙንም ገልጸዋል።

አሁን ላይ 12 መስኖ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ቀሪዎቹም በሂደት ወደ ስራ ይገባሉ ብለዋል።

በበጋ የመስኖ ስራ በአትክልት፣ ፍራፍሬና ስራስር ሰብሎችን ለማምረት መደበኛ የመስኖ ስራ ገቢራዊ የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመደበኛ መስኖ አትክልት፣ ፍራፍሬና ስራስር ልማት እስካሁን 349 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ 89 በመቶው በዘር ስለመሸፈኑም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰዋል።

በበጋ የመስኖ ስንዴ 400 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 16 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት የታቀደ ሲሆን እስካሁን 256 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ 64 በመቶው በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።

ከበጋ መስኖ ልማት ባሻገር የመኸር ምርት ጥራትን በጠበቀ መልኩ እንዲሰበሰብ በቴክኖሎጂ ታግዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተፋስስ ልማት የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ በአረንጓዴ አሻራ ለአገር በቀልና ለምግብነት የሚውሉ የእፅዋት ዝርያዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም