አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጫና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ከተማ እየተካሄደ ነው

195

ታህሳስ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገው ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ ዋይት ሃውስ ፊት ለፊት እየተካሄደ ነው።

"የበቃ ወይም #NoMore" ዘመቻ አካል በሆነው ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እየተሳተፉ መሆኑን ኢዜአ ከሰልፉ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ሰልፈኞቹ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ እየተከተለ ያለውን የተሳተተ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲያስተካክልና ጣልቃ ገብነቱን እንዲያቆም ጥሪ የሚያደርጉ መልዕክቶች እያስተላለፉ ነው።

ሰልፈኞቹ አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ጥቃት የሚያወግዙና ለኢትዮጵያ አጋርነታቸውን የሚያሳዩባቸው መፈክሮች እያሰሙ ነው።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የዳያስፖራ ማህበረሰብና የሲቪክ ተቋማት ተወካዮች፣ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው አፍሪካውያንና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ንግግር እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለውን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲያስተካልና ጣልቃ ገብነቱን እንዲያቆም ጫና ለማድረግ ሰላማዊ ሰልፉ በዋሺንግተን ዲሲ በቋሚነት በየሳምንቱ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ያለው ሰላማዊ ሰልፍ ሰላምና አንድነት ማህበር የዋሺንግተን ዲሲ ግብረ ሃይል ከ "በቃ ወይም #NoMore" ዘመቻ አስተባባሪዎች፣ ከተለያዩ ተቋሞችና አገር ወዳዶች ጋር በመተባባር ያዘጋጁት ነው።

አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በተለያዩ አገራት ከተሞች እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም