የሶስት ዓመት ልጄ ላይ መሳሪያ አቀባብለው በመደገን ደፍረውኛል

629

ታህሳስ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎች የሶስት ዓመት ልጄ ላይ መሳሪያ አቀባብለው በመደገን ደፍረውኛል – የግል ተበዳይ።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በወልድያ ከተማ ያልሰራው ወንጀል ያልፈጸመው ነውር የለም።

ንጹሐንን በአደባባይ ረሽኗል፣ የመንግስት ተቋማትና የግለሰብ ሀብት ዘርፏል፣ ሴቶችን ደፍሯል።

የወልድያ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወጣት የሽብር ቡድኑ ሰይጣናዊ ተግባር ሰለባ ሆናለች።

ተበዳይዋ እንደምትለው “ነሀሴ 7 ቀን 2013 ምሽት ላይ ዝናብ እየዘነበ ነበር፣ በቁጥር በርከት ብለው ወደ ቤት መጡ፣ ዝናቡን ለማሳለፍ እንደሆነ ነገሩኝ፣ ከደቂቃ በኋላ ቤት መግባት እንደሚፈልጉ ሲነግሩኝ አልከፍትም አልኳቸው፣ ክብሪት ጠየቁኝ በበሩ ስር አሾልኬ ሰጠኋቸው ቆይተው የተደበቀ ወታደር ካለ ልናይ ነው ክፈችው እያሉ በሩን በሀይል መደብደብ ጀመሩ” ትላለች።

ባለቤቷን ከአንድ ዓመት በፊት በሞት እንዳጣችና ከሶስት ዓመት ልጇ ጋር እንደምትኖር ብትነግራቸውም መስማት አልፈለጉም።

በመጨረሻም በሩን ሰብረው በመግባት ያለውን ነገር ከፈተሹ በኋላ ሰው ሲያጡ የሶስት ዓመት ህጻን ልጄ ጭንቅላት ላይ መሳሪያ አቀባብለው አስገድደው ደፈሩኝ ብላለች።

በወቅቱ ከኔ ጋር ለማደር የመጣችን የ14 ዓመት ልጅ ከተዘጋ የጎረቤት ቤት በመውሰድ ለአራት ደፍረዋታል ብላለች።

ህፃኑ ልጅ በወቅቱ የነበረው ሰቆቃ አልረሳ ብሎት ሌሊት ይቃዣል፣ መሳሪያ የያዘ ሰው ሲያይ በድንጋጤ እያለቀሰ የስነልቡና ጫና ተፈጥሮበታል ብላለች።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።