ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን እንፋለማለን በጽኑ እናወግዛለን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን እንፋለማለን በጽኑ እናወግዛለን

ወይዘሮ ካሰች መንግስቴ የዕድሜያቸው መግፋት ነፍጥ አንስተው አሸባሪውን ህወሃት ለመፋለም ባያስችላቸውም ቡድኑ ወረራ ፈጽሞባቸው በነበሩት የአማራና አፋር ክልሎች በዜጎች ላይ በተለይም በህጻናትና በሴቶች ላይ የፈጸመውን ግፍና ሰቆቃ ለማውገዝ አልሰነፉም።
ከሰው ልጅ አልፎ በቤት እንስሳት ላይ ጠመንጃ አንስቶ ግድያ የፈፀመን የህወሃት አሸባሪ ቡድን ሁላችንም በቻልነው ሁሉ በጋራ ልንታገለው ይገባል የሚሉት ወይዘሮ ካሰች፤ ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ ተገኝተው የአሸባሪውን ድርጊት አውግዘዋል።
አሸባሪውን ህወሃት በህጻናትና በሴቶች ላይ እየፈጸመ ያለውን አስገድዶ መድፈርና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲሁም የአንዳንድ ምዕራባውያን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነትን የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሂዷል።
በሰልፉ ላይ ከወጣት እስከ አዛውንት እንዲሁም አካል ጉዳተኞች ጭምር የአረመኔውን የህወሃት አሸባሪ ቡድን እኩይ ተግባር ለማውገዝ ከማለዳው ጀምሮ በመስቀል አደባባይ ተገኝተዋል።
ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል የእድሜ ባለጸጋዋ ወይዘሮ ካሰች መንግስቴ አይነ ስውር ቢሆኑም አሸባሪው ህወሃት በሴቶችና ህፃናት ላይ እየፈፀመ ያለውን አስነዋሪና አሰቃቂ ድርጊት ሰምቼ ዝም አልልም በማለት ለተቃውሞ ወጥተዋል።
በሽብር ቡድኑ ቤተሰቤን ተነጥቄያለሁ የሚሉት እናት "ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን አቅሜ ቢፈቅድ በግንባር እፋለመው ነበር፤ ይህንን ማድረግ ባልችልም ማውገዝ አያቅተኝም" ብለዋል።
በሰልፉ ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ ወጋየሁ መኩሪያ፤ አሸባሪው ቡድን በወረራ በያዛቸው በአፋርና አማራ ክልሎች በእናቶች፣ ህጻናትና አረጋዊያን ላይ የፈፀመው ድርጊት ሁላችንንም አሳዝኖናል ብለዋል።
አንዳንድ የዓለም አገራትና የምዕራባዊያኑ መገናኛ ብዙሃን ይህንን ድርጊት በቅጡ ማውገዝ ሲገባቸው ዝምታን መርጠው ይባስ ብሎ በመንግስት ላይ ጫና ማሳደራቸው ተገቢ አለመሆኑን አንስተዋል።
ከአፋር ክልል ክልል መጥተው በሰልፉ ላይ የተገኙት ወይዘሮ ነስሩ ዑዳ፤ አሸባሪው ህወሃት በአፋርና አማራ ክልሎች በሰው ልጆች ላይ ሊደረግ ቀርቶ ሊታስብ የማይችል ዘግናኝ ግፍ ፈጽሟል ብለዋል።
ቡድኑ በደረሰበት ሁሉ ሴቶችና ህጻናትን በመድፈር፣ ሰላማዊ ዜጎችን በመግደልና ንብረት በመዝረፍ እንዲሁም በማውደም የቻለውን ሁሉ ግፍ ፈፅሟል ሲሉ ተናግረዋል።
የሽብር ቡድኑ ይህንን ሁሉ ግፍና በደል እየፈፀመ ለመብትና ለሰው ልጆች ደህንነት እንቆረቆራለን የሚሉት አንዳንድ ምእራባዊያን በዝምታ ማለፋቸው በእጂጉ አሳዛኝ ነው ብለዋል።
የሽብር ቡድን እስከሚጠፋ የሚችሉትን ሁሉ አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆነናቸውን አረጋግጠዋል።
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።