በባህር ዳር ከተማ የሴፍቲኔት ልማት ፕሮግራም ተጀመረ

150

ባህር ዳር ፤ ታህሳስ 10/2014(ኢዜአ) በባህር ዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ 3 ሺህ 935 ወገኖችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሴፍቲኔት ልማት ፕሮግራም ተጀመረ።


የከተማዋ አስተዳደር  ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ  ዶክተር ድረስ ሳህሉ በወቅቱ እንደገለጹት፤ፕሮግራሙ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና አለው።

እንዲሁም የባህርዳር  የአረንጓዴ ውበትን በማሳደግ የቱሪዝም ከተማነቷን ከማሳደጉም ባሻገር ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ፕሮግራሙ  በተቀመጠለት እቅድ መሰረት እውን እንዲሆንና  ዜጎች በተገቢው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተማ አስተዳደሩ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ስራና ክህሎት ስልጠና ቢሮ ሃላፊ አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ በክልሉ 17 ከተሞች  የሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ታቅፈው ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ሲከናወን መቆየቱንተናግረዋል።

አሁን ላይ የባህር ዳር ከተማ በይፋ የተጀመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአሸባሪው የህወሃት ቡድን ወረራ ነፃ በሆኑ ሽዋ ሮቢት፣ ከሚሴ፣ ኮምቦልቻን ጨምሮ 10 ከተሞችም ፕሮግራሙ  እንደሚጀምርም ጠቁመዋል።

በሽብር ቡድን ወረራ ውስጥ የቆዩ ሌሎች 7 ከተሞች ከወረራ ሙሉ በሙሉ ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

ሃላፊው እንዳሉት፤ ፕሮግራሙ በከተሞች መስራት እየቻሉ በድህነት የሚኖሩ ወገኖችን በአረንጓዴ ልማትና ማስዋብ ስራ በማሳተፍ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደርጋል።

በተለይም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ቀጥታ ድጋፍ እንደሚያገኙ አስረድተዋል።

ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያም ከመንግስትና የአለም ባንክ ለአንድ ዓመት  ከ200 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞ እየተተገበረ መሆኑም ተመልክቷል።

''በከተማው 3ሺህ 935 ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ደጋፊና ጧሪ የሌላቸው አረጋዊያን በፕሮግራሙ ታቅፈው ተጠቃሚ ይሆናሉ'' ያሉት ደግሞ የከተማዋ አስተዳደር  የፕሮግራሙ አስተባባሪ ወይዘሮ እመቤት መንግስቱ ናቸው።

የመስራት አቅም ያላቸውና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ  ዜጎች በከተማ ፅዳትና ውበት እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ስራ እንደሚሰማሩ ገልጸው፤  መስራት የማይችሉ አረጋዊያን ደግሞ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው ያሉት።

ባህር ዳር ካላት ውበት በተሻለ መልኩ የከተማዋን ፅዳትና ውበት በማስጠበቅ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የኑሮ ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ፕሮግራሙ  ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።

በክልሉ በመጀመሪያው ዙር  ደሴ ከተማ በፕሮግራሙ  ታቅፎ የቆየ ሲሆን ዛሬ የተጀመረው የባህር ዳርን ጨምሮ ሌሎች ከተሞች  በሁለተኛው ዙር  ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም