አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ተቋማትና ንብረት አውድሟል

77

ሰመራ፣ ታህሳስ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል ወረራ በፈጸመበት ወቅት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ተቋማትንና ንብረት ማውደሙ ተገለጸ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በትምህርት ሴክተር ዙሪያ ከአፋር ክልል  ከፍተኛ አመራሮች ጋር በሰመራ ከተማ  ተወያይተዋል።

አሸባሪው ቡድን የትምህርት ሴክተሩን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ በጥናት እንደተረጋገጠ በውይይት መድረኩ ተመልክቷል።

በመድረኩ  ጽሁፍ  ያቀረቡት በክልሉ ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ  አቶ ጌታሁን አስራት እንደገለጹት፤ በክልሉ በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት የትምህርት ዘርፍ ማህበረሰብ  ለከፍተኛ ችግር ተጋልጧል።

የሽብር ቡድኑ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች በሚገኙ  21 ወረዳዎች 759 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ150 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ ማድረጉን አስረድተዋል።

65 ትምህርት ቤቶች በሽብር ቡድኑ ሙሉ በሙሉ የወደው ሲሆን 138 የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ወድመዋል ያሉት ባለሙያው፤ በክልሉ ያሎ፣ ጉሊና፣ እዋ፣ አውራ፣ ቴሩና ጭፍራ ወረዳዎች ከፍተኛውን ጉዳት ማስተናገዳቸውን ገልጸዋል።

የትምህርት ተቋማቱ በከባድ መሳሪያ ጭምር ድብደባ ተፈጽሞባቸው እንዲወድሙ መደረጉን ጠቅሰዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ  በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሃት በንጹሃን ዜጎች ላይ ከፈጸመው ጭፍጨፋና ማፈናቀል ሌላ የንብረት ውድመትና ዘረፋ መፈጹሙን ጠቅሰዋል።
 
ቡድኑ የመንግስት ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ  ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ባለሙያዎች ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት ተረጋግጧል ብለዋል።

የደረሰውን ውድመት መልሶ በማቋቋም ተቋማትን ወደስራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ትምህርት ትውልድ ለመቅረጽ ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያመለከቱት።

የሽብር ቡድኑ በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ የከፈተው ጦርነት በዚህ የተወሰነ  ሳይሆን  እንደሀገር ኢትዮጵያን ለማፍረስና ዜጎቿንም ለሰቆቃ ለመዳረግ ያለመ እኩይ ሴራ ነው ያሉት ደግሞ  የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ናቸው።

በቡድኑ ጥፋት ጉዳት ለደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች የአፋር ክልል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን እንደሀገር መልስ የሚሰጠው ይሆናል ብለዋል።

ለዚህም የሚረዳ የሃብት ማፈላለግና ማሰባሰብ ስራዎች የተለያዩ አጋር አካላትን በማሳተፍ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም