ከጋምቤላ ክልል 540 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ቀረበ

143

ጋምቤላ (ኢዜአ) ታህሳስ 10/2014 ---የጋምቤላ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ 546 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አኳታ ቻም ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ከክልሉ ባለፉት አምስት ወራት ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው ወርቅ በባህላዊ የወርቅ አምራቾች የተመረተ ነው።   

በሀገሪቱ ላይ እየተደረገ ያለውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋምና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ለማዕድን ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ሀገር አሁን እየተደረገባት ባለው የውጭ ጫና የሚገጥማትን ፈተና ለመቋቋም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።   

ዳይሬክተሯ እንዳሉት ባለፉት አምስት ወራት ለዘርፉ በተደረገ ክትትልና ድጋፍ በዲማ፣ በአበቦ፣ በጋምቤላና በመንጌሽ ወረዳዎች 546 ኪሎ ግራም ወርቅ በባህላዊ አምራቾች ተመርቶ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል።

ለባንኩ ገቢ የተደረገው የወርቅ ምርትም ከ23 ሚሊዮን 216 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ከክልሉ ዘንድሮ የተመረተው የወርቅ ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ50 ኪሎ ግራም ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።  

የድጋፍና ክትትል ሥራዎችን በማጠናከር በበጀት ዓመቱ እስከ 1ሺህ 600 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ  መታቀዱንም አስታውቀዋል።

በጋምቤላ ወረዳ ቦንጋ ቀበሌ በባህላዊ ወርቅ ማምረት ሥራ ከተሰማሩት መካከል ወጣት ታሪኩ መንግስቴ እንዳለው በቀን ከሁለት እስከ ሦስት ግራም ወርቅ በአማካኝ በማምረት እስከ 4ሺህ ብር ገቢ እያገኘ ነው።

በወርቅ ማዕድን ቁፋሮ በቀን ከ6 እስክ 10 ግራም ወርቅ የሚገኝበት ሁኔታ እንዳለ የገለጸው ደግሞ ሌላው የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ተመስገን ተክሉ ነው።

ከክረምት ይልቅ በአሁኑ ወቅት የተሻለ የወርቅ ምርት እያገኙ ቢሆንም የአንድ ግራም የመሸጫ ዋጋው ከሦስት ሺህ ወደ ሁለት ሺህ 800 ዝቅ በማለቱ ተጠቃሚነታቸው መቀነሱን ተናገሯል።

በዚሁ ቀበሌ በወርቅ ግብይት ከተሰማሩት መካከል አቶ ገብረህይወት  ዮሐንስ ባለፉት አምስት ወራት ከአራት ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች ተረክብው ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

"በአምራቾች በኩል የወርቅ የመግዣ ዋጋ መጠነኛ ቅናሽ አለ" በሚል ለተነሳው ቅሬታም ባንኩ የሚያወጣው የዋጋ ተመን እንጂ በእነሱ በኩል የመቀነስም ሆነ የመጨመር ስልጣን እንደሌላቸው ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል በቀዳሚው ዓመት በባህላዊ ወርቅ አምራቾች 1ሺህ 212 ኪሎ ግራም ወርቅ ተመርቶ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም