በጋምቤላ ከተማ ህግ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የተደረሰባቸው ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

67

ጋምቤላ፣ ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጋምቤላ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ በጋምቤላ ከተማ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የተደረሰባቸውን ሁለት ተጠርጣሪዎች ዛሬ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን አስታወቀ።

የኮሚቴው አባልና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በክልሉና የፌዴራል ፖሊስ የተቀናጀ ጥረት ነው።

ኮሚሽነሩ እንዳሉት፤ ተጠርጣሪዎቹ በጋምቤላ ከተማ ህገወጥ የጦር መሳሪያ በባጃጅ ተሽከርካሪ በማጓጓዝ ላይ እንዳሉ ተደርሶባቸው ነው።

ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ከተጠርጣሪዎቹ ዘጠኝ ክላሽንኮቭ መያዙን ጠቁመዋል።

ግለሰቦቹ ቁጥጥር ስር ውለው ተጨማሪ የማጣራት ስራ እየተከናወነ ሲሆን፣ እንደተጠናቀቀም ጉዳያቸው ለፍርድ ቤት ይላካል ብለዋል።

በቁጥጥር ስራ ከዋሉት ግለሰቦች መካከል አንዱ ቀደም ሲል የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪ ነው በሚል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በዋስ ተለቆ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሂደት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ኅብረተሰቡ ተጠርጣሪዎቹን ከነጦር መሳሪዎቹ ለመቆጣጠር ያደረገውን ትብብር ወደፊትም አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽነር አቡላ አሳስበዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም