አሸባሪው የህወሃት ቡድን ወልዲያ በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት እጅግ አሰቃቂ ግፍ ሲፈጽም ቆይታል

74

ታህሳስ 9/2014 (ኢዜአ)አሸባሪው የህወሃት ቡድን ወልዲያ በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት እጅግ አሰቃቂ ግፍ ሲፈጽም ቆይታል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

የአሸባሪ ቡድኑ ወራሪ ኃይሎች በከተማዋ ሴቶችን አስገድደው በመድፈር፤ሰላማዊ ዜጎችን በጅምላ በመጨፍጨፍና ንብረት በማውደም ግፍ መፈጸማቸውንም ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ወልዲያን ጨምሮ የሰሜን ወሎ ዞንን ሙሉ በሙሉ ከአሸባሪው ህወሃት ወረራ ነጻ ማውጣቱ ይታወቃል።

የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች አሸባሪ ቡድኑ ወደ ከተማዋ ከገባበት እለት ጀምሮ የሰቆቃ ጊዜ እንዳሳለፉ ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

የአሸባሪ ቡድኑ ወራሪ ኃይሎች "በርካታ ወጣቶችን በአደባባይ በግፍ ገድለዋል፤ሴቶችን በቡድን ደፍረዋል፤የግለሰቦችን ቤት በየቀኑ እየፈተሹ ሃብት ንብረት ዘርፈዋል" ነው ያሉት ነዋሪዎቹ፡፡

የወልድያ ሆስፒታል እና ዩኒቨርስቲን ጨምሮ የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና የፋይናንስ ተቋማት ሙሉ በሙሉ መዘረፋቸውንም ገልጸዋል።ኢትዮጵያውያን ወገኖች አዲስ ዓመትን ሲያሳልፉ እኛ በጨለማ ውስጥ ነበርን ብለዋል።

''የእኛ አዲስ ዓመታችንና ዳግም ውልደታችን ዛሬ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ፣የሽብር ቡድኑ ለዓዕምሮ የሚከብድ ወንጀል ፈጽሟልም '' ብለዋል።

በከተማዋ በርካታ ወጣቶች በአደባባይ በግፍ መገደላቸውንም ገልጸዋል።የሽብር ቡድኑ መንገድ ላይ የሚለምኑ ሰዎችን ሳንቲም ጭምር በመውሰድ የነውረኝነቱን ጥግ አሳይቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም