በአሸባሪው ቡድን ተፈናቅለው በሸዋ ሮቢት ከተማ ለሚገኙ ወገኖች 20 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

215

ደብረ ብርሃን፤ ታህሳስ 9/2014(ኢዜአ) በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ወረራ ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሽዋ ሮቢት ከተማ ለሚገኙ ወገኖች 20 ሚሊየን ብር የሚገመት የምግብ እህል እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሶች ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ያደረጉት ኮፓሽን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅት ከመሰረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የእርዳታና ልማት ማህበር ጋር በመተባበር ነው።

የኮፓሽን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የሰሜንና ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የአጋርነት ስራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ ከበደ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት፤ ድርጅቱ በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አሰባስቧል።

እስካሁንም ከደጋፊ አካላት በተሰባሰበው 100 ሚሊዮን ብር በአፋር እና አማራ ክልል ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የመሰረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እርዳታና ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻምቡ ባልቻ በበኩላቸው፤ የተደረገው ድጋፍ ህፃናትን ጨምሮ ከ21 ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለአንድ ወር ቀለብ የሚሆን ነው ብለዋል።

በቀጣይም ማህበረሰቡ የአካባቢውን ልማት ተሳታፊና ወደ ቀድመው ኑሮ እንዲመለስ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ዘነበ ተክሌ ፤ የከተማው ህዝብ በጦርነቱ ሳቢያ ለዘመናት ሰርቶ ያካበተው ሃብት ተዘርፏል ብለዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖች አሁን ላይ ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው መኖር መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ በከተማው 60 ሺህ ህዝብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ድጋፍ ያስፈልገዋል ነው ያሉት።

ዛሬ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያልተቋረጠ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖች የመደገፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጪ ቡድን መሪ አቶ ደረጀ ይንገሱ ናቸው።

አሁን ላይ ከ240 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተፈናቃይ ወገኖች የአንድ ወር ቀለብ መከፋፈሉን ጠቅሰው፤ በቀጣይም አቅም በፈቀደ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

አሁን ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ በጦርነቱ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ከጊዜያዊ ድጋፍ ባለፈ በዘላቂነት ለማቋቋም በመንግስት በኩል ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከተፈናቃይ ወገኖች መካከል አቶ መሃመድ አሊ በሰጡት አስተያየት፤ አሸባሪው ቡድን በፈፀመው ዝርፊያ ለችግር መጋለጣቸውን ጠቅሰው፤ አሁን የተደረገላቸው ድጋፍ ጊዜያዊ ችግራቸውን እንደሚያቃልልላቸው ተናግረዋል።

ወይዘሮ አሰገደች ሀይለስላሴ በበኩላቸው፤ በሽብር ቡድኑ የጥፋት ተግባር ምክንያት ቤተሰባቸው ለችግር መጋለጡን አመልክተዋል።

የተደረገው ድጋፍ ከወደቅንበት እንድንነሳ የሚያግዘን ነው፤ ቀጣይም ችግሩ እስኪፈታ መሰል ድጋፍ እንፈልጋለን ብለዋል።