በህገ-ወጥ መታወቂያ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመጠቀም በሚሞክሩ ተሳፋሪዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል

335

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በህገ-ወጥ መታወቂያ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመጠቀም በሚሞክሩ ተሳፋሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ የተሳፋሪዎች ከመታወቂያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚታዩ ክፍተቶችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የድርጅቱ የህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አምባቸው፣ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረው ድርጅቱ በየእለቱ ከ90 እስከ 100 ሺህ ለሚጠጉ ለአዲስ አበባ እና ለፌደራል የመንግስት ሰራተኞች የደርሶ መልስ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

አገልግሎቱ እየተሰጠ ያለው ህጋዊ የሆነ የድርጅቱ መታወቂያና የሚሰሩበት ተቋም መታወቂያ ላላቸው የመንግስት ሰራተኞች መሆኑንም አክለዋል።

ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህጋዊው መታወቂያ ተመሳስሎ እየተሰራ እንደሚገኝና ህጋዊ መታወቂያው ጭምር ሙሉ ማንነታቸውን መግለጽ እስከማይቻል ድረስ ተበላሽቶ ጥቅም ላይ ሲውል ታይቷል ብለዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ተሳፋሪዎች የአገልግሎት ጊዜያቸው የተጠናቀቀ መታወቂያዎችን ሲጠቀሙበት ይታያል ነው ያሉት።

አያይዘውም አንዳንድ ተሳፋሪዎች ህጋዊ መታወቂያው ላይ የሚገኘውን ፎቶ በመቀየር ጭምር አገልግሎት ለማግኘት ሲሞክሩም እንደሚታዩ ጠቅሰዋል።

በተጠቀሱት ምክንያቶች ከ200 በላይ መታወቂያዎች፣ ተሳፋሪዎች በሚያደርጉት ጥቆማ እና በድንገተኛ ፍተሻ ተይዘዋል ብለዋል።

በዚህም ህገ-ወጥ የፐብሊክ ሰርቪስ  መታወቂያ ይዘው በተገኙ ተሳፋሪዎች ላይ በፀጥታ አካላት ክስ ተመስርቶባቸው ክትትል እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በቀጣይም ድርጅቱ በህገ-ወጥ መልኩ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማግኘት በሚሞክሩ ተሳፋሪዎች ላይ እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት።

ከዚህ በኃላ በሁለት ወር አሊያም በሶስት ወሩ ድንገተኛ ክትትል እንደሚደረግም  ነው ያስታወቁት።

ሕጋዊ ተሳፋሪዎችም በህገ-ወጥ መንገድ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚሞክሩ ተሳፋሪዎችን እንዲከላከሉ እና ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።