በቁጥጥር ግኝት ተገቢው እርምትና ማስተካካያ እንዲወሰድ የምክር ቤቱ እገዛ አስፈላጊ ነው -ተቋሙ

116

አዳማ፤ ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተቋማት የቁጥጥር ግኝት መሰረት ተገቢው እርምትና ማስተካካያ እንዲወሰድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እገዛ አስፈላጊ መሆኑን የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ።

የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት በሚችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲሱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አመራሮች ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ መክሯል።

የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ በወቅቱ እንደገለጹት ተቋሙ የህዝብና የመልካም አስተዳደር በደሎች እንዳይፈፀሙ የተሰጠውን ስራ በአግባቡ መወጣት እንዲችል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እገዛ ወሳኝ ነው።

በተለይ አስፈፃሚው አካላት የአስተዳደር በደሎች እንዳይፈጽሙና ፈፅመው ከተገኙም አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ በየጊዜው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በተቋማቱ ላይ በሚደረግ የቁጥጥር ግኝትና ግብረ መልስ መሰረት በአስፈፃሚው አካላት ላይ  ተገቢው እርምትና ማስተካካያ እየተወሰደ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

በቁጥጥር ግኝት መሰረት ተገቢው እርምትና ማስተካካያ እንዲወሰድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እገዛ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

"የመልካም አስተዳደር በደሎች ላይ ህዝቡ ቅሬታ እያነሳ ነው" ያሉት ዶክተር እንዳለ ቅሬታውን ለመፍታት ተቋሙ የምክር ቤቱን እገዛ  እንደሚፈልግ አስታውቀዋል።

አብዛኛው የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ዘንድ ከለውጡ ወዲህ የቁጥጥር ግኝቱን ግበረመልስ ለመፈፀም ፍላጎት ቢኖርም ተባባሪ በማይሆኑ ላይ የእርምት እርምጃን ጨምሮ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር መተግበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

"በተለይ በየአመቱ በልዩ ሪፖርት ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚላኩ ከ30 እስከ 40  አቤቱታዎች እየተፈቱ አይደለም " ያሉት ዶክተር እንዳለ አቤቱታዎቹ የበርካታ ዜጎችን ጉዳይ የያዙ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

"የምክር ቤቱ እገዛ ወሳኝ ነው" ያሉት ዶክተር እንዳለ የክትትልና ቁጥጥር ግኝቶች የፖሊስና የህግ ማእቀፍ ማሻሻያ የሚያስፈልጉም ከሆነ ምክር ቤቱ መፍትሄ ሊሰጥበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተለይ በማዘጋጃ ቤቶች፣ ለልማት ተነሺዎችና ለልማት ፕሮጄክቶች በሚሰጥ የመሬት ካሳ ክፊያ እንዲሁም በኤሌክትሪክ አገልግሎትና በፍትህ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን  አስታውቀዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ በበኩላቸው " ከተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል።

"ተቋሙ በክትትልና ቁጥጥር ስራው የፍትህ መጓደል፣ አስተዳደራዊ በደሎች ዙሪያ የሚሰጣቸው ግብረ መልሶችና የጥናቱ ግኝቶች በአስፈፃሚው አካላት ተገቢውን ትኩረት አግኝተው ማስተካካያ ሊደረግባቸው ይገባል" ያሉት ሰብሳቢዋ ምክር ቤቱም ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

"የቁጥጥር ውጤቶች  በተቋማቱ  አካባቢ የሚታዩ የአሰራር፣ የአስተዳደራዊ በደሎችና የፍትህ መጓዳል ክፍተቶች ናቸው" ያሉት ወይዘሮ እፀገነት ተቋማቱ የሚሰጧቸው ግብረ መልሶች ላይ አፋጣኝ ማስተካከያዎች መውሰድ እንደሚገባቸው አስገዝበዋል።

"የምንፈልገውን ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት ለመገንባት አስፈፃሚው አካላት ለሚሰጣቸው የቁጥጥር ግኝት ግብረ መልስ አስቸኳይ መፍትሄና እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል" ሲሉ ወይዘሮ እፀገነት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም