የግብጽ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና አጀንዳ በመስጠት ተጠምደዋል

79

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) ''የግብጽ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና አጀንዳ በመስጠት ተጠምደዋል" ሲሉ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአረብኛ ቋንቋ መምህርና የአረብ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚዲያ ዳሰሳ በማድረግ የሚታወቁት አቶ ኡመር መኮንን ገለጹ።

አቶ ኡመር መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት  አብዛኛው የግብጽ መገናኛ ብዙሃን በተለይ ጋዜጦቻቸው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ አሉታዊና የተዛቡ መረጃዎችን እያሰራጩ አንደሚገኙ አንስተዋል።

እነዚህ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨትን የዘወትር ተግባራቸው ማድረጋቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

የዘገባዎቻቸው ዋነኛ ዓላማም በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ጫና እንዲፈጠር ማድረግ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በግብጽ ሰፊ ስርጭት ያለው አህራም ጋዜጣን ጨምሮ እንደ አሽሩቅ፣አልጀሙሪያ፣አል-ሙስጠቅበል አል-ሱልጣን፣ ሰደል-በለድና ሌሎችም በርካታ ጋዜጦች ላይ ኢትዮጵያ የእለት ተእለት አጀንዳቸው መሆኗን ነው የሚገልጹት፡፡

ጋዜጦቹ በዋናነት "በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ሰላም እንደሌለ" በማስመሰል ኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲበረታ ለማድረግ የሚተጉ ስለመሆኑም አቶ ኡመር ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጅምላ ግድያዎች በስፋት እየተከናወነ በማስመሰል ትንተና ማቅረብ ደግሞ የግብጽ ጋዜጦች ዋነኛ መታወቂያ መሆኑን አቶ ኡመር አብራርተዋል።

እነዚህ መገናኛ ብዙሃን በአሸባሪው የህወሃት ቡድን የሚፈጸሙ ዘግናኝ ግፎችን በምንም መልኩ ማንሳት እንደማይፈልጉ ገልጸው፤ በዚህም የአረቡ ዓለም ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሳሳተ ምልከታ እንዲኖረው ይሰራሉ ነው ያሉት፡፡

የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ለአንዳንድ የምእራባዊያን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሳሳተ አጀንዳ  እንደሚሰጡም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በአረበኛ ቋንቋ ተደራሽነታቸውን በማስፋት ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጪነት መሸጋገር እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡

በዚህ ረገድ ምሁራን ወደ መገናኛ ብዙሃን በመቅረብና በተለያዩ ቋንቋዎች የኢትዮጵያን እውነት በማሳወቅ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ሴራ መመከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም