አፍሪካን ተጽእኖ ፈጣሪ ለማድረግ በጋራ መቆም አማራጭ የሌለው መንገድ ነው

438

ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) አፍሪካን ተጽእኖ ፈጣሪ ለማድረግ በጋራ መቆም አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ እና እስያ ጥናት ምርምር ተቋም መምህር ዶክተር መሃመድ ሃሰን ተናገሩ።

አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ኢትዮጵያ ያራመደችውን ጽኑ አቋም ሁሉም የአፍሪካ አገራት አጀንዳቸው አድርገው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የአፍሪካዊያን በጋራ መቆም ተሰሚነታቸውንና ተጽእኖ ፈጣሪነታቸውን ለማሳደግ ሁነኛ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ማግኘት አለባት የሚለውን ትግል መቀላቀላቸውን መግለጻቸው በሌሎች የአፍሪካ አገራት ዘንድ መነቃቃትን መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ የተጀመረው እንቅስቃሴ ለሁሉም እኩል የሆነች ዓለም እንድትኖር ከመሻት የተነሳ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተጀመረው እንቅስቃሴ የፍትህ፣ እኩል የመሆን እና የነጻነት ትግል በመሆኑ ሁሉም አፍሪካዊያን ድምጻቸውን አጉልተው ማሰማት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።  

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻነት እንዲረጋገጥ በሄደችበት መንገድ ዛሬም ይህ ጥያቄ በእሷ በኩል መነሳቱ ትግሏ የመላ አፍሪካዊያን ትግል ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።  

ይህ የአሁኑ አጋጣሚም ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን የኢትዮጵያን የመቻል እና የማድረግ ታሪካዊ ሂደት የሚያሳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።  

”የምዕራቡን ዓለም ተንኮልና ሴራ ለማክሸፍ አፍሪካዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን ማጠናከር አለባቸው” የሚሉት ዶክተር መሃመድ፤ በተናጠል ትግል ከግብ የሚደርስ ጥያቄ እንደሌለ አብራርተዋል።

አፍሪካዊያን አንድነታቸውን ማጠናከር ካልቻሉ የምዕራባዊያን መጠቀሚያ ይሆናሉ ሲሉም ነው የገለጹት፡፡   

ዶክተር መሃመድ አክለውም፤ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ እና ይህ ጥያቄ ከግብ እንዲደርስም ኢትዮጵያዊያን የጀመሩትና አፍሪካዊያን እየተቀላቀሉት ያለው የ “#በቃ” ንቅናቄ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

አፍሪካዊያን አንድነታችውን አጠናክረው ከተናጠል ይልቅ በጋራ ድምጻቸውን ካሰሙ ጥያቄያቸው መልስ የሚያገኝበት ሩቅ እንደማይሆንም ጠቁመዋል።     

ኢትዮጵያ የተቃጣባትን ሁሉን አቀፍ ዘመቻ በመመከት አፍሪካን ከዘመናዊ ቅኝ ግዛት ነጻ ለማውጣት የጀመረችው ትግልም ለአፍሪካውያንና ለሌሎች ጭቁን ህዝቦች መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑንም ተጠቁመዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።