የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያካሄደው ልዩ ስብሰባ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚያደርጉ አካላት ጉዳይ ማስፈጸሚያ ነው

70

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ትናንት ያካሄደው ልዩ ስብሰባ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚያደርጉ አካላት ጉዳይ ማስፈጸሚያ በመሆኑ ውሳኔውን ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ውሳኔ እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸው መንግስት ውሳኔውን የማይቀበል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ባለፉት ሶስት ዓመታት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ከፍተኛ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አንስተው፤ ከዚህ አኳያ የምክር ቤቱ ውሳኔ  በኢትዮጵያ ያለውን ሃቅ የካደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመሆን ግልጽና ገለልተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

መንግስት በዚህ ሪፖርት መሰረት የተገኙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እርምት እርምጃ ለመውሰድ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ሆኖም ኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ማስፈጸም የሚሹ አካላት ዳግም ይህን ሃሳብ ማንሳታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን በወረራ በያዛቸው የአማራ እና አፋር ክልሎች ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጽም ዝምታን የመረጡ አካላት አሁን በዚህ መልኩ መምጣቸው የራሳቸውን ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም ሥለማቀዳቸው ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ አሸባሪው ሕወሃት በአፋር እና በአማራ ክልል ዘግናኝ የሰብዓዊ ጥሰት በፈፀመበት ወቅት መከናወኑም አግራሞትን ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

በስብሰባው ላይ የምክር ቤቱን ውሳኔ የደገፉ አንዳንድ አገራት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃለመግባት የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የቆዩ መሆናቸውንም ነው ያነሱት፡፡   

የምክር ቤቱ ውሳኔ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚያደርጉ አካላት ጉዳይ ማስፈጸሚያ መሆኑ በግልጽ መታየቱን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ውሳኔውን እንደማትቀበለው ተናግረዋል፡፡

በስብሰባው ከኢትዮጵያ ጎን ለነበሩ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁንም በገለልተኝነት፣ ህጋዊ ሂደቱም በጠበቀ መልኩ እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ ምርመራ የሚያደርጉ ገለልተኛ አካላት ካሉ በሮቿ ክፍት መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም