በኢትዮጵያ በበጋ መስኖ ከሚለማው ስንዴ ከ18 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል-ሚኒስቴሩ

106

ጎንደር፣ ታህሳስ 09/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዘንድሮ በበጋ ወቅት በመስኖ ከሚለማው ስንዴ ከ18 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የግብርና ሚኒስትር አስታወቀ።

በማእከላዊ ጎንደር ዞን በምስራቅና ምእራብ ደንቢያ ወረዳዎች ክልል አቀፍ የበጋ ወቅት መስኖ ስንዴ ልማት የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ዛሬ ተካሂዷል።

ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር መለሰ መኮንን በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት በተያዘው ግብ መሰረት በዘንድሮ የበጋ መስኖ 400 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

ልማቱ በዋናነት እየተካሄደባቸው ባሉ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሶማሌና በሲዳማ ክልሎች ለበጋ ወቅት እስካሁን 154 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

"በመኽር የእርሻ ሥራ ላይ ጥገኛ የሆነውን የአገሪቱን ግብርና ለማሻሻል በዓመት ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ በመስኖ በማልማት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ሚኒስቴሩ በሃገራዊ የመስኖ ስንዴ ልማቱ እየተሳተፉ ለሚገኙ ክልሎች ከበጀት ጀምሮ የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ግብአቶችን በማቅረብ አገራዊውን ግብ ለማሳካት ጥረት እያደረገ መሆኑን ዶክተር መለሰ አስታውቀዋል።

''በአማራ ክልል በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 80 ሽህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል'' ያሉት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማርያም ከፍያለው ናቸው።

ስንዴ አልሚ አርሶ አደሮችን በምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦት እንዲሁም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየታገዙ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በክልሉ በተቀናጀ አግባብ ከሚለማው መሬት 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አመልክተዋል።

''ተመፅዋች ሃገርና ህዝብ ጉልበትም ክብርም የለውም''ያሉት ሃላፊው፣ "አርሶ አደሩ በዓላትንና ድግስን በመቀነስ በምግብ እህል ራስን ለመቻል ሌት ተቀን መስራት ይጠበቅበታል" ሲሉም አስገንዝበዋል።

የማእከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ በበኩላቸው በዞኑ በበጋ መስኖ 6 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ እንደሚለማ አመልክተዋል።

''በበጋ መስኖ ስንዴን ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ማልማት ጀምሬያለሁ''ያሉት ደግሞ በዞኑ የምስራቅ ደምቢያ ወረዳ የአዲስጌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፈንቴ ካሴ ናቸው።

ከሚለማው መሬት እስከ 50 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ያመላከቱት አርሶ አደሩ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም