ከአፍሪካ ጋር ያለንን ትብብር በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ እንዲያድግ እንሰራለን -ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን

77

ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከአፍሪካ ጋር ያለን ትብብር በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ እንዲያድግ እንሰራለን ሲሉ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን አስታወቁ።

ሶስተኛው የቱርክ- አፍሪካ ትብብር ጉባኤ በቱርክ ኢስታንቡል በመካሄድ ላይ ነው።

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ቱርክ እ.አ.አ ከ2005 ጀምሮ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በአዲስ አካሄድ መቃኘቷን አስታውሰው ይህም ከአፍሪካ ጋር ያለንን ወዳጅነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ከአፍሪካ ጋር የሚኖረንንም ግንኙነት “በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ እንዲያድግ እንሰራለን፣ ትስስሩ ሁሉም አሸናፊና ተጠቃሚ የሚሆንብት እንዲሆን ነው የምንሰራው” ብለዋል።

“አህጉሯን በሚጎዳ፣ ተገቢ ያልሆነና የግል ተጠቃሚነትን ብቻ የሚከተል አካሄድን ሁሌም ውድቅ በማድረግ ነው ከአፍሪካ ጋር ያለንን ግንኙነት የምናሳድገው” ሲሉም ገልጸዋል።

ቱርክ ከአፍሪካ ጋር ላላት ወዳጅነትና ስትራቴጂካዊ አጋርነትም ከአፍሪካ ህብረት ጋር በጋራ ለመስራት ያካሄደችውን ስምምነት ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራት መሪዎች በ3ኛው የቱርክ-አፍሪካ ትብብር የመሪዎች ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው።

-አካባቢህን ጠብቅ፣ _

ወደ ግንባር ዝመት፣ _

መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም