በዞኑ ለህልውና ዘመቻው የስንቅ ዝግጅቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል

50

መተማ፣ ታህሳስ 9/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ስንቅ ተዘጋጅቶ ለፀጥታ ኃይሉ ወደ ግንባር መላኩን የዞኑ ሎጅስቲክ አቅርቦት አስተባባሪ ገለጹ።

አስተባባሪዋ ወይዘሮ ደመቅ አበባው ለኢዜአ እንደገለጹት የህልውና ዘመቻው ስኬታማ እንዲሆን በዞኑ የስንቅ ዝግጀቱ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የስንቅ ዝግጅቱ መላ ህብረተሰቡን፣ የመንግስት ሠራተኞችን፣ መምህራንንና ሴቶችን በማሳተፍ በተጠናከረ አግባብ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዘመቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነትን ተከትሎ ውጤት መሰማቱ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩንም ገልጸዋል።

በግንባር እየተፋለመ ላለው የወገን ጦር አጋርነትን ለማሳየት ከመንግሥት ሠራተኞች በተጨማሪ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ያለማንም ቀስቃሽ በስንቅ ዝግጅት ሥራው እየተሳተፈ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዞኑ ሲቪል ሰርቪስ የሰው ኃይል አስተዳደር መምሪያ ባለሙያ ቀሲስ ፈንታሁን ቢሆነኝ በበኩላቸው የህልውና ዘመቻውን በድል ለመወጣት ያልተቆጠበ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ ለህልውና ዘመቻው ገንዘብ በማዋጣት ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ እኔ በየትኛው ግንባር ነኝ በሚል ደጀንነቱን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የስንቅ ዝግጅቱ በትኩረትና በተጠናከረ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የመተማ ወረዳ መሬት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ባለሙያ ወይዘሪት ሶሎሜ ሰማ ናቸው።

በጦር ግንባር የህይወት መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለ ያለውን የፀጥታ ኃይል በስንቅ መደገፍ ግዴታ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይም አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ ባለፉት ሁለት ወራት 26 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ስንቅ የተዘጋጀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 17 ሚሊዮን ብር የሚገመተው በግንባር ለሚገኘው የፀጥታ ኃይል መላኩ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም