ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ጥቅሟና ፍላጎቷ ውጪ የፖለቲካ ፍላጎትን ለመጫን የሚከናወኑ ማንኛውም ድርጊቶችን አትቀበልም

263

ታህሳስ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ጥቅሟና ፍላጎቷ ውጪ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ሊጭኑባት የሚፈልጉ ሃይሎችን ድርጊት እንደማትቀበል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በእውነትና መርህ ላይ ተመስርተው ድጋፍ እያደረጉ ላሉ ወዳጅ አገራት ሚኒስቴሩ ምስጋና አቅርቧል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ዙሪያ ያካሄደውን ልዩ ስብሰባና በምክር ቤቱ የጸደቀውን የውሳኔ ሀሳብ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም ኢትዮጵያ ምክር ቤቱ አንዳንድ አገራት የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያና መጠቀሚያ መሆኑ እጅጉን እንዳሳዘናት ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ እንዳይካሄድ ሲገልጽና ሲቃወም የነበረ ቢሆን ይሄንን ችላ በማለት ስብሰባው መካሄዱን አመልክቷል።

ስብስባው ምክር ቤቱ ያጸደቀውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የጋራ ሪፖርት ግኝት ያላከበረና የናቀ መሆኑን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ዙሪያ ያካሄደውን ልዩ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትና ነጻነት የሚገዳደር ነው ብሏል።

ኢትዮጵያም ያለ ፍላጎቷና ፈቃዷ በተደረገው ልዩ ስብሰባ የተላለፈውን ውሳኔ እንደማትቀበል፣ እንደማትፈጽምና የትኛውንም አይነት ትብብር እንደማታደርግ ነው መግለጫው ያመለከተው።

ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ጥቅሟና ፍላጎቷ ውጪ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለመጫን የሚከናወኑ ማንኛውም ድርጊቶችን እንደማትቀበል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስገንዝቧል።

በሰብአዊ መብት ስም በአገራት ላይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነትና ፖለቲካዊ ጫና ሊቆም ይገባል ብሏል።

በእውነትና መርህ ላይ ተመስርተው ልዩ ስብሰባውንና የውሳኔ ሀሳቡን በመቃወም ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም አጋርነታቸውን ላሳዩ አገራት ምስጋና አቅርባለች።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕግ የዜጎች ሰብአዊ መብቶች እንዲጠበቁና እንዲከበሩ ያሉባትን ግዴታዎች ለመወጣት አሁንም በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ሚኒስቴሩ በመግለጫው አስታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ያቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ 15 አገራት ተቃውመዋል።

ምክር ቤቱ ያቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ከተቃወሙት 15 አገሮች በተጨማሪ 11 አገሮች ድምጸ ተዓቅቦ አድርገዋል።ኤርትራ፣ ሕንድ፣ ጋቦን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ቻይና፣ ናምቢያ፣ ቬንዙዌላ፣ ኩባ፣ ፓኪስታን፣ ፊሊፒንስ፣ ሶማሊያ፣ ሩሲያ፣ ካሜሮን፣ ኮትዲቭዋርና ቦሊቪያ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡን የተቃወሙ አገራት ናቸው።

በረቂቅ የውሳኔ ሀሳቡ ላይ ድምጸ ተዓቅቦ ያደረጉ 11 አገራት ደግሞ ሊቢያ፣ ማላዊ፣ ሱዳን፣ ሴኔጋል፣ ቶጎ፣ ሞሪታኒያ፣ ባህሬን፣ ባንግላዴሽ፣ ኔፓል፣ ኡዝቤኪስታንና ኢንዶኔዢያ ናቸው።

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ላይ የጠራውን ልዩ ስብሰባ 13 የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ 22 የምክር ቤቱ አባል አገራት እንደተቃወሙት ይታወቃል።