አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት አሸባሪው በንጹሃን ላይ እየፈጸመ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዳላዩ ማለፋቸው የሚወገዝ ነው

77

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 08/2014 (ኢዜአ) አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራትና የሰብዓዊ መብት ተቋማት አሸባሪውን ህወሓት በንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዳላዩ ማለፋቸው የሚወገዝ መሆኑ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ ገለጹ።

የአሸባሪው ህወሓት የጭካኔ ድርጊትና የአንዳንድ ምዕራባዊን  ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ክልል አቀፍ ሰልፍ  ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በተካሄደበት ወቅት የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደተናገሩት፤ ሀገር ለማፍረስ የተነሳው  አሸባሪው ህወሓት በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በተለይ በሴቶችና ህፃናት ላይ ጭካኔ የተሞላበት  ግፍ ፈጽሟል።

ድርጊቱ እጅግ  ዘግናኝ መሆኑን ጠቁመው፤ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ አንዳንድ ሴቶች    ህይወታቸውን እስከ ማጥፋት መድረሳቸው ተናግረዋል።

አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራትና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማቶቻቸው የአሸባሪውን ህወሓት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ከማውገዝ ይልቅ በቸልተኝነት ማለፋቸው የሚወገዝ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የሀገራቱንና የመገናኛ ብዙሃኑን ፀረ-ኢትዮጵያ አቋምና  ጣልቃ ገብነት  የሚያሳይ  መሆኑን ያመለከቱት።

በአሸባሪው ህወሓት ወረራ  ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን  የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሠላማዊና የተረጋጋ ህይወት እስኪጀምሩ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ በበኩላቸው፤አሸባሪው ህወሓት በእናቶችና በህጻናት ላይ  ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት እየፈፀመ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በውጭና በሀገር ውስጥ ሆነው ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎች በሲዳማ ሴቶች ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ሰናይት አረታ በሰጡት አስተያየት፤ የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች አዛውንቶችን ጭምር በመድፈር የጭካኔ ተግባር መፈጸማቸው አሳዛኝ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።

በህፃናት ላይም የተፈጸመው ዘግናኝ ግፍ  የሚኮነን መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ሰናይት፤ ይህንን እኩይ ተግባር ለማውገዝና አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ ለመጠየቅ  በሰላማዊ ሰልፉ ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራትና የውጭ መገናኛ ብዙሃን የአሸባሪው ህወሓትን ግፍ በቸልተኝነት በመላፍ መወገናቸው እንዳሳዘናቸው  በመግለጽ አውግዘዋል፡፡

በሰልፉ ላይ ተሳታፊ የነበረችው ተማሪ ህይወት መንገሻ በበኩሏ፤ አሸባሪው ህወሓት በትምህርት ተቋማት ላይ ባደረሰው ውድመት ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መስተጓጓላቸው እንዳሳዘናት ተናግራለች።

የወደሙ ትምህርት ቤቶች ዳግም ተገንብተው ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ሁሉም አካል እንዲረባረብ ጠይቃለች።

በሰልፉ ላይ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ  አደረጃጀቶች የተውጣጡ ሴቶች፣ ተማሪዎችና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም