የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት መርሳና ግራናን በመቆጣጠር ወደፊት እየገሠገሠ ነው

217

ታህሳስ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት መርሳና ግራናን በመቆጣጠር ወደፊት እየገሠገሠ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት፣ በዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ በቆቦ ግንባር ቀደም ብሎ የዞብል ከፍተኛ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ የነበረ ሲሆን፣ የቁጥጥር አድማሱን በማስፋት በራያ ሰሜናዊ አቅጣጫ ያሉትን ከፍተኛ ቦታዎችን ጨምሮ ተቆጣጥሯል፡፡

በዞብል ደቡብ አቅጣጫ ደግሞ የጉራ ወርቄ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የነበረው የወገን ጦር፣ አሁን ደግሞ የጉራ ወርቄ ከፍተኛ ሰንሰለታማ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ በማጽዳት፣ ቀደም ብሎ የተቆረጠውን የወልድያ መቀሌ መሥመር አሰፋፍቶ፣ ወደ ወልድያ በቅርብ ርቀት እየገሠገሠ ይገኛል፡፡

ባለፈው ጊዜ ውጫሌ ከተማን ነጻ ያወጣው የወገን ጦር፣ በዚሁ ግንባር የውጫሌ ወረዳን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረ ሲሆን የውርጌሳ፣ የሊብሶ፣ የግራና፣ የመርሳ፣ የኪሌ ከተሞችንና በሰሜን ወሎ የሐርቡ ወረዳን ከፍተኛ ሰንሰለታማ ተራሮችን በእጁ አስገብቷል፡፡

በእነዚህ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ጀግኖቹ የወገን ጥምር ጦር በንሥሮቹ አየር ኃይላችን በመታገዝ ጠላትን ከመርሳ በስተጀርባ ቆርጠው በመግባት፣ በውጫሌና በውርጌሳ መካከል ተከማችቶ የነበረውን ጠላት ሙሉ በሙሉ ደምስሰውታል፡፡

የአካባቢው ኅብረተሰብም ከወገን ጥምር ጦር ጋር በመቀናጀት፣ እግሬ አውጪኝ ብሎ የሚሸሸውን ጠላት ከየጢሻው እየመነጠረ በመደምሰስ፣ አኩሪ ጀብድ ፈጽሟል፡፡

የኀብረተሰቡና የወገን ጦር ቅንጅት ጠላት የዘረፈውን ንብረትና ተተኳሾቹን ይዞ መውጣት እንዳይችል አድርጎታል፡፡

የወገን ጥምር ጦር በወልድያና ሐራ ከተሞች መካከል የሚገኘውንና መውጫ ያጣውን ጠላት በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ በማጥቃት ላይ ይገኛል፡፡ ነጻነታችንን የምናስከብረው በተባበረ ክንዳችን ነው!የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት