የቬትናሙ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ሽኝት ተደረገላቸው

68
አዲስ አበባ ነሐሴ 19/2010 በኢትዮጵያ የነበራቸው የሶስት ቀናት ጉብኝት ውጤታማ እንደነበረ የቬትናሙ ፕሬዝዳንት ትራን ዳይ ኳንግ ተናገሩ። ፕሬዝዳንቱ የሶስት ቀናት የኢትዮጵያ ቆይታቸውን አጠናቀው ዛሬ ረፋዱ ላይ ወደ ግብጽ ሲያቀኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ሸኝተዋቸዋል። ኳንግ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የነበራቸው ቆይታ ውጤታማና የተሳካ ነበር። በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ ሁለቱ አገራት በጋራ ሊሰሩባቸው የሚችሉ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያውያን ባለስልጣናት ጋር በተደረገ ውይይት ስምምነት ላይ ለመድረስ ተችሏል ብለዋል። ስምምነት በተፈረመባቸውና መግባባት ላይ በተደረሱባቸው የኢንቨስትመንትና የንግድ የጋራ ትብብር ላይ ለመስራት እንደሚፈልጉም ነው የተናገሩት። ኢትዮጵያና ቬትናም ተመሳሳይ የሆነ የነፃነት መለያና ታሪክ ያላቸው አገራት እንደመሆናቸው ለራሳቸውና ለጎረቤቶቻቸው ሰላም መጠበቅ በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አስታውቀዋል። ቬትናም  በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ለመክፈት እንደምትፈልግም ተናግረዋል። ሰሞኑን በነበራቸው ምክክርም የአገራቱን የምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ አሁን ካለው 11 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ ቬትናም ፍላጎት እንዳላት ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት። በአገራቱ መካከል በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት ከዚህ ቀደም የተፈረሙ ስምምነቶች ወደተግባር እንዲቀየሩም ቬትናም ትሰራለች ብለዋል። ቬትናም በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይም ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ መስራት እንደምትፈልግ ፕሬዝዳንት ትራን ዳይ ኳንግ መናገራቸው ይታወሳል። የሁለቱ አገራት ፓርላማዎችም በመረጃና ልምድ ልውውጥ እንዲሁም በህግ አወጣጥ ላይ ተባብረው እንደሚሰሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የቬትናም ፕሬዝዳንት ትራን ዳይ ኳንግ ከፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ውይይት ማካሄዳቻው ይታወቃል። በእስካሁኑ ቆይታቸው የኢትዮጵያና የቬትናም ግንኙነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ስምምነቶች ተፈርመዋል። ኢትዮጵያና ቬትናም በይፋ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር መጋቢት 1976 ነው። ፕርዝዳንቱ አሁን ላይ ወደ ግብፅ ያቀኑ ሲሆን በግብጽም ተመሳሳይ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም