የኢትዮጵያን ከፍ ወዳለ የክብር ማማ ጉዞ መገስገሷን ማንም ሊስቆማት አይችልም- ኢንጂነር አይሻ መሀመድ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ከፍ ወዳለ የክብር ማማ ጉዞ መገስገሷን ማንም ሊስቆማት አይችልም- ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

ባህር ዳር፣ ታህሳስ 8/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ከሀዲነቱን ቢያስመሰክርም የኢትዮጵያን ከፍ ወዳለ የክብር ማማ ጉዞ መገስገሷን ማንም ሊስቆማት አይችልም ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ።
አሸባሪ ቡድኑ በአማራ ክልል በሴቶችና ህፃናት ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍና ፆታዊ ጥቃት የሚያወግዝ ሰልፍ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደበት ወቅት ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ቡድኑ የአማራና የአፋር ክልልን በመውረር ማዕከላዊ መንግስቱን ለመቆጣጠር ቢጥርም በወገን ጥምር ማክሸፍ ተችሏል።
"ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በህጻናትና አዛውንቶች ላይ አሰቃቂ ግፍና ፆታዊ ጥቃት ፈፅሟል፤ እየፈፀመም ይገኛል" ብለዋል።
አሸባሪው ቡድን ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ከሀዲነቱንና ባንዳነቱን ቢያስመሰክርም ኢትዮጵያን ከፍ ወዳለው የክብር ማማ መገስገሷን ማንም ሊያስቆማት አይችልም ነው ያሉት።
ዓለም አቀፍ የፀረ- ፆታ ጥቃት ቀንን ምክንያት በማድረግ እየተካሄደ ያለው ሰላማዊ ሰልፍ በሴቶችና ሕጻናት ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ለማውገዝና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድምጽን ለማሰማት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
"አሸባሪው ህወሓት የለኮሰውን ጦርነት በፍጥነት በማጠናቀቅ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል" ብለዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው፤የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት ሴቶች፣ ህፃናትና አረጋዊያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለጥቃት፣ ለእንግልትና ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን ነው የገለጹት።
"ስለ ሰብዓዊ መብት ጥበቃና ስለዴሞክራሲ የሚሰብኩን አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት የህወሓትን ወንጀል አልሰሙም፣ ቢሰሙም ለማስቆም ምንም ፍላጎት የላቸውም" ያሉት ደግሞ የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ ናቸው።
ይልቁንም ህወሓት የሚፈጽመው ጥቃትና ወንጀል እንዲቀጥል በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው፣" ስለ ሰብዓዊ መብት የሚሰብኩን አካላት በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፋቸውን ነፍገዋል" ብለዋል።
በሴቶችና ህፃናት ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና በደል እስኪቆም ድረስ ድምጽን ከፍ አድርጎ ማሰማት እንደሚቀጥል ገልጸው፤ አሸባሪው በየትኛውም ሀገርና ጊዜ ያልተደረገ አሰቃቂ ወንጀል በንጹሀን ዜጎች ላይ እየፈፀመ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሰልፉ ዓላማ በአሸባሪውና ወራሪው ቡድን እየተፈፀሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎችን ለማውገዝ፣ አጥፊዎችም በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲጠየቁ ለማድረግ እና የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ጣልቃ ገብነትን ለመቃወም መሆኑን አስረድተዋል።
ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ቻይና አያሌው፤አሸባሪው ህወሓት በእናቶችና ህጻናት ላይ እየተፈጸመ ያለውን የጭካኔ ተግባር በአደባባይ ለማውገዝ ሰልፍ መውጣታቸውን ተናግረዋል።
"ህወሓት በህፃናትና መነኮሳት ላይ ሳይቀር እየፈፀመ ያለው አስነዋሪ ተግባር ማስቆም ይገባል'' ብለዋል።
በሰልፉ ላይ የተሳተፉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም "በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቁም! ፣ ፆታዊ ጥቃት የሚፈፅመውን ወራሪ ቡድን አጥብቀን እናወግዛለን!" ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።