የአየርላንድ መንግስት የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግስት ፍላጎት ማክበር አለበት

251

ታህሳስ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአየርላንድ መንግስት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግስትና የሕዝቡን ፍላጎት ማክበር እንዳለበት በአየርላንድ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት ገለጹ።

የ’በቃ’ ወይም ‘#NoMore’ ዘመቻ አካል የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በአየርላንድ መዲና ደብሊን ‘ትሪኒቲ ኮሌጅ’ በማድረግ ወደ አየርላንድ ፓርላማና አሜሪካ ኤምባሲ በማቅናት መካሄዱን ‘ቮይስ ፎር ኢትዮጵያ አየርላንድ’ የተሰኘው ግብረ ሃይል አባል ወይዘሮ ራሔል ዳልተን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ሰልፉ አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም እንደሆነ አመልክተዋል።

ሰልፈኞቹ አየርላንድ በኢትዮጵያ ያልተገባ ጫና ለማሳደር ያደረገችው እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለውና ኢትዮጵያውያውያን እንደማይቀበሉት ማስገንዘባቸውን ተናግረዋል።

የአየርላንድ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የያዘውን የተሳሳተ ፖሊሲ እንዲያርም ጥሪ መቅረቡንና የአየርላንድ መንግስት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግስትና የሕዝቡን ፍላጎት ማክበር እንዳለበት መግለጻቸውን ጠቅሰዋል።

በሰልፉ ላይ ‘በቃ’ ወይም ‘#NoMore’ መፈክሮች መስተጋባታቸውንና በአየርላንድ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን መሆናቸውን በተግባር ማሳየታቸውን አመልክተዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በአየርላንድ ደብሊን፣ ኮርክ፣ ጋሎዌይና ሊምሪክ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና የአየርላንድ ዜጎች  ተሳትፈዋል።

ከሰልፉ ባለፈ ለአየርላንድ ባለስልጣናት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የማስረዳትና ለፓርማላ አባላት ደብዳቤ በመጻፍ የመሞገት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው ወይዘሮ ራሔል የተናገሩት።

በአየርላንድ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በአሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ የተፈናቀሉ ዜጎችን መርዳት ጨምሮ ለሌሎች ወቅታዊ አገራዊ ጥሪዎችና የልማት ፕሮጀክቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በአየርላንድ የሚካሄደውን የ’በቃ’ ወይም ‘#NoMore’ ዘመቻ ሰላማዊ ሰልፍ ያዘጋጁት ‘ቮይስ ፎር ኢትዮጵያ አየርላንድ’ የተሰኘው ግብረ ሃይል ከአገር ወዳድ ግለሰቡ አቶ ሃይማኖት አይናለም ጋር በመሆን እንደሆነ ተገልጿል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።