አፍሪካዊያንን በማሳተፍ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ ጣልቃገብነት ለማስቆም እየሰራን ነው

79

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) "አፍሪካዊያን በማሳተፍ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ ጣልቃገብነት ለማስቆም እየሰራን ነው" ሲሉ በደቡብ አፍሪካ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባልና የዩናይትድ ሚዲያ ሃውስ መስራች አቶ በኃይሉ መሃመድ ገለጹ።

በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ በተባበረ ክንድ እየመከቱት ይገኛሉ፡፡

በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣው ዘመቻ ዘርፈ ብዙ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በሁሉም ግንባሮች ተሰልፈው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እያበረከቱ ነው፡፡

በውጭ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን የተጀመረው "#በቃ" ዘመቻ ደግሞ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ሲሆን፤ አፍሪካዊያንና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ዘመቻውን በስፋት እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡

በደቡብ አፍሪካ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባልና የዩናይትድ ሚዲያ ሃውስ መስራች የሆኑት አቶ በኃይሉ መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለመመከት ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ እየሰራ ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን የውጭ ጣልቃ-ገብነት በሚመለከት ለአፍሪካዊያን የግንዛቤ መፍጠር ተግባር ሲያከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በቅርቡም በደቡብ አፍሪካ የተባበሩት የኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ ማህበር ከአፍሪካ ዳያስፖራ ፎረም ጋር በመተባበር ከገንዘብ መዋጮ ጀምሮ አገራቸውን ለመደገፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

ከሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት "#በቃ" ዘመቻ አካል የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ በአገሪቱ መዲና ፕሪቶሪያ መካሄዱንም ገልጸዋል፡፡

በሰልፉ "የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካዊያን ይፈታል" የሚለውን እሳቤ በተግባር ያሳየ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ላደረገላቸው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አፍሪካዊያንን በማሳተፍ ዘመቻው ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በቁርጠኝነት እየሰሩ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

በዚህም በደቡብ አፍሪካና ደቡባዊ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገሪቱ ባሉ ስመ-ጥር መገናኛ ብዙሃን በመቅረብ በአገራቸው ያለውን እውነት እያሳወቁ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ዳያስፖራው በአሸባሪው ህወሃት ወረራ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት ረገድ የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም