ሆስፒታሎቹ የወደሙ የህክምና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚያግዝ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

71

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዳግማዊ ምኒልክ ኮንፕሪንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና የጥሩነሽ ቢጅንግ ጠቅላላ ሆስፒታል በአሸባሪው ህወሃት ወረራ የወደሙ ሆስፒታሎችን መልሶ ለማቋቋም የሚረዳ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

አሸባሪው ህወሃት በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በፈጸመባቸው አከባቢዎች ባደረሰው ውድመት እስካሁን ባለው መረጃ ከ2 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑ የጤና ተቋማት ላይ ዘረፋና ውድመት ፈጽሟል፡፡

በዚህም የጤና ሚኒስቴር በግጭቱ አካባቢ ፈጣን ዳሰሳ በማካሄድ አሁን ላይ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እና ስራ ለማስጀመር እጅግ ከፍተኛ ሃብት እንደሚያስፈልግ ማረጋገጡን አመላክቷል፡፡

በጤና ተቋማቱ ላይ በተከሰተዉ መጠነ ሰፊ ውድመት፤ በርካታ ዜጎች  የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት አግባብ በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ተስተጓጉሏል፡፡

በተጨማሪም የአሸባሪው ህወሃት ቡድን የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አምቡላንሶችን ዘርፏል፤ መውሰድ ያልቻላቸውን ደግሞ አውድሟል፡፡

ይህን ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የድንገተኛ አደጋ የጤና ምላሽ ስርዓት አቋቁሞ ዘርፈ ብዙ ርብርብ እያደረገ ይገኛል።

ሚኒስቴሩ የተዘረፉና ውድመት የደረሰባቸዉን የጤና ተቋማት ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጋር በማጣመር  መልሶ ለማቋቋም እና ስራ ለማስጀመር ግብ አስቀምጦ እየሰራ ነው፡ ፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮም ጥሪውን ተቀብሎ በአሸባሪ ቡድኑ የተጎዱ የጤና ተቋማትን በመለየትና በመዲናዋ የሚገኙ የጤና ተቋማትን ከአጋሮቹ ጋር በማስተሳሰር ድጋፍ ማድረግ ጀምሯል፡፡

ይህን ተከትሎ የጥሩነሽ ቤጅንግ አጠቃላይ ሆስፒታልና ዳግማዊ ምኒልክ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል  የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ጀምረዋል፡፡

የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል መልሶ ለማቋቋም ለተረከበው የኬሚሴ ሆስፒታልና ጤና ጣቢያ ማስጀመሪያ የሚሆን ድጋፍ አድርጓል።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ኢሉባቡር ቡኖ የተረከቡትን ጤና ተቋም መልሶ ለማቋቋም ሆስፒታሉ 15 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።

በተመሳሳይ የዳግማዊ ምኒልክ ኮንፕሪንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መልሶ ለማቋቋም የተረከበውን የመሃል ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራ ለማስጀመር ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ታደሰ ሃይለየሱስ ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቁት።

የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ደሴ ሆስፒታልን፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከልዋን ሆስፒታልን እና ቦሩ ሜዳ ሆስፒታልን፣ አቤት ሆስፒታል ባቲ ሆስፒታልን መልሶ የማቋቋም ኃላፊነት ወስደዋል፡፡

በተጨማሪ የካቲት 12 ሆስፒታል ወረኢሉ ሆስፒታን፣ ምኒሊክ ሆስፒታል መሃል ሜዳ ሆስፒታልን፣  ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሀይቅ ሆስፒታልን፣ ራስ ደስታ ሆስፒታል ደብረ ሲና ሆስፒታልን መልሶ ለማቋቋም ደጋፍ የሚያደርጉ ይሆናል፡፡

ከዚህ ባለፈም አለርት ሆስፒታል ኮምቦልቻ ሆስፒታልን፣ ዘውዲቱ ሆስፒታል ደጎሎ ሆስፒታልን፣ ጋንዲ ሆስፒታል ሞላሌ ሆስፒታልን የሚደግፉ ሲሆን፤ አማኑኤል ሆስፒታል ደግሞ ሁሉም ሆስፒታሎች የአእምሮ ጤናና የስነ-ልቦና ድጋፍ እንደሚያደርግ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም