አዲሱ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ የውጭ ምንዛሬ እንዳይባክንና ተጠያቂነትን ለማስፈን ያስችላል

191

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬን በተመለከተ በቅርቡ ያወጣው መመሪያ የውጭ ምንዛሬ እንዳይባክንና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል መሆኑን የዘርፉ ምሁር ጠቆሙ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀምን በተመለከተ አዲስ መመሪያ በቅርቡ  አውጥቷል። መመሪያው አዳዲስ አሰራሮችን ይዞ መጥቷል ተብሏል።

በተለይም ባንኮች ከሚያቀርቧቸው የውጭ ምንዛሬ አገልግሎቶች 50 በመቶ የሚሆነው መንግሥት ትኩረት ባደረገባቸው ፕሮጀክቶች ላይ መዋል እንዳለባቸው ያስገድዳል።  

ቀሪውን ደግሞ ባንኮቹ በፈለጓቸው የሥራ መስኮች ማዋል የሚችሉ ሲሆን ያልተጠቀሙበትን የውጭ ምንዛሬ ደግሞ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረግ እንዳለባቸው ደንግጓል።

ባንኮቹ የውጭ ምንዛሬ ቅድሚያ ማግኘት ያለባቸው ሴክተሮች የለየ ሲሆን በመጀመሪያ ደረጃ የፋርማስዩቲካልና የምግብ ዘይት ግብዓቶች እንዲሁም ነዳጅ ይገኙበታል።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለግብርና ለአምራች ኢንደስትሪዎች ግብዓትነት ግዥ የሚውሉ የውጭ ምንዛሬዎች መፈቀድ እንዳለበት መመሪያው አቅጣጫ አስቀምጧል።

በሦስተኛ ደረጃ ወደ የሞተር ዘይትን ጨምሮ በርካታ ለሕክምና ላብራቶሪ፣ ለግብርና፣ ለትምህርት፣ ለአምራች ዘርፉና ሌሎችም ሴክተሮች ትኩረት መደረግ እንዳለበት አመላክቷል።

መመሪያውም የውጭ ምንዛሬን በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስችል ነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር ብርሃኑ ደኑ የሚናገሩት።

በተለይም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ የውጭ ምንዛሬን እጥረት መኖሩን ገልጸው ያለውነ ውስን ኃብት ከብክነትን ለመከላከልና ፍሰቱንም ለመቆጣጠር አመቺ መመሪያ ነው ብለዋል።    

በተጓዷኝም የውጭ ምንዛሬ ሕገ-ወጥ በሆነ መልኩ ከአገር እንዳይወጣና የማይሆን ዘርፍ ላይ እንዳይውል በማድረግም አሰራር አቅጣጫ ማስቀመጡን አንሰተዋል።

ይህም በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ላይ ግልጸኝነት በማስፈን ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።    

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም የውጭ ምንዛሬ እጥረት የነበረባቸው ዘርፎች ለአብነትም የምግብ ዘይት አማራቾች በመጀመሪያ ደረጃ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ መደረጉን የሚበረታታ ነው ብለዋል።

እነዚህም ዘርፎች ምርትና ምርታማነታቸውን በማስፋት ከውጭ ተመሳሳይ ምርት ለማስገባት  የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደሚቻልና ይህም ትልቅ እምርታ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግሥት በሌሎች ዘርፎች ላይ የአገር ውስጥ ምርት እንዲስፋፈ ለማድረግ የሚያከናውነውን ተግባራት ይበልጥ በማጠናከር ለውጭ ምንዛሬ እጥረት መፍትሄ ማምጣት እንደሚገባ አሳስበዋል።