ኮርፖሬሽኑ ለአፋር ክልል ተፈናቃይ ወገኖች ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

143

ሰመራ ታህሳስ 8/2014 (ኢዜአ)የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ፣ አልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ኮርፖሬሽኑ ተፈናቃዮቹን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ የድርሻውን እንደሚወጣ ተመላክቷል።
 

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ድጋፉን ከኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን  ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዱካን ደበበ ዛሬ ተረክበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ኮርፖሬሽኑ ያደረገው ድጋፍ በአሸባሪው ህወሓት ከቤትና ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ችግር  የሚያቃልል መሆኑን በመግለጽ ምሰጋና አቅርበዋል ።

ኢትዮጵያውያን ለተፈናቃዮች እያደረጉ ላለው ድጋፍ አድናቆታቸውን የገለጹት ርእሰ መስተዳደሩ

ተፈናቃዮችን ከደረሰባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለማውጣት የቆየው የመረዳዳት ባህል እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

አቶ ሳንዶካን ደበበ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ሀገር የመታደግ ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጓዳኝም በአሸባሪው ቡድን የጥቃት ሰለባ የሆኑ ወገኖችን በመደገፍ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል።

በክልሉ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ የድርሻውን እንደሚወጣም አመላክተዋል ቃል ገብተዋል።

ኮርፖሬሽኑ ያደረገው ድጋፍ አልባሳት፣ የማብሰያና መገልገያ ቁሳቁስ፡ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያዎች እንዲሁም የህጻናት አልሚ ምግብና የታሸገ ውሀ ያካተተ መሆኑ ተመላክቷል ።