አሸባሪው ህወሃት በአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ ኮምቦልቻ ማዕከል እና በጎሽ ሜዳ ፕላስቲክ ፋብሪካ በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት ጉዳት አድርሷል

196

ታህሳስ 08/2014(ኢዜአ) አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ ኮምቦልቻ ማዕከል እና በደሴ ጎሽ ሜዳ ፕላስቲክ ፋብሪካ በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት ጉዳት እንዳደረሰባቸው ድርጅቶቹ አስታወቁ።

ከአማራ ህዝብ ሃብት ከሆኑ ድርጅቶች መካከል የአማራ ደን ልማት ኢንተርፕራይዝ ኮምቦልቻ ማዕከል የእንጨት መሰንጠቂያ ፋብሪካ በዚህ ዓመት ወደ ሥራ መመለስ በማይችልበት ደረጃ ሙሉ በሙሉ ውድመትና ዘረፋ እንደደረሰበት ሥራ አስኪያጁ አቶ አያሌው ዮሴፍ ገልጸዋል።

ድርጅቱ ካሉት ቋሚ ሰራተኞች ባሻገር ከ300 በላይ ለሚሆኑ ግብዓት አቅራቢ አርሶአደሮች የሥራ ዕድል ፈጥሮ እንደነበር ገልጸዋል።

በድርጅቱ እስከ 8 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ በርካታ ማሽኖች ዘረፋና ውድመት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በደሴ ከተማ በስተደቡብ ምዕራብ በሚገኘው ጎሽ ሜዳ የአማራ ፕላስቲክና ቧንቧ ፋብሪካ ከ125 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ዘረፋና ውድመት ፈጽሟል።

የድርጅቱ የማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አራጌ የምስራቅ አማራ ውሃ አጠር አካባቢዎችን ችግር ለመቅረፍ በ2011 ዓ.ም ወደ ሥራ የገባው ፋብሪካው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ውድመትና ዘረፋ ተፈጽሞበታል ብለዋል።

ፋብሪካው አራት አይነት የፕላስቲክና ቧንቧ ምርቶችን እንደሚያመርትና ከ70 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩንም አስታውሰዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ፋብሪካው የሠራተኞች ቢሮ እንኳን እንዳይኖረው አድርጎ ውድመት መፈጸሙንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ድርጅት ግቢ ውስጥ የሚገኘው የአማራ ህንፃ ስራዎች ድርጅት የደሴ ግንባታ ግብዓት ማዕከልም በመቶ ሚሊዮኖች የሚደርስ ጉዳት እንደደረሰበት ተገልጿል።