የአገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን የኢኮኖሚ ጫና ማክሸፍ ይገባል

167

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 08/2014(ኢዜአ) የአገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀምና የውጭ ምንዛሬን በመቆጠብ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን የኢኮኖሚ ጫና ማክሸፍ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

“የኢትዮጵያን እንግዛ”  በሚል መሪ ቃል ለስድስት ቀናት የሚቆይ ኤግዚቢሽንና አውደርዕይ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

ኤግዚቢሽንና አውደርዕዩ በመዲናዋ በተለያዩ ስድስት ቦታዎች የተከፈተ ሲሆን፤ ከአራት መቶ በላይ የዘርፉ ተዋናዮች ምርቶቻቸውን ከማቅረብ ባሻገር የኪነ-ጥበብ ስራዎችም ይቀርቡበታል ተብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አስፋው ለገሰ እንደተናገሩት፤ ኤግዚቢሽኑ የገበያ ትስስርን ከመፍጠር ባለፈ የአገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህል እንዲጎለብትና የአገር በቀል እውቀቶች እንዲስፋፉ ያግዛል፡፡

የአውደ ርዕዩ ዓላማ የከተማዋን የቱሪስት ሃብቶች በማልማትና በማስተዋወቅ የዘርፉን ገቢ በማሳደግ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን የኢኮኖሚ ጫና መቋቋም እንደሆነም ጠቁመዋል።፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዳያስፖራዎች የመዲናዋን የቱሪስት ሃብቶች ለማስጎብኘት ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ዲያስፖራው የአገሩን ምርት ገዝቶ ለሌሎች እንዲያስተዋውቅ እድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡

በስፍራው የተለያዩ የአገር ውስጥ ምርቶችን ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሃይማኖት ታደሰ በአገር ልጅ የተመረተ ምርት በመግዛታቸው መደሰታቸውን  ገልጸዋል፡፡

በኤግዚብሽኑ ላይ የቀረቡ ምርቶች በጥራትና ደረጃቸው ተወዳዳሪ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ምርቶቹ ከውጭ የሚመጣን እቃ የተሻለ አድርጎ በማሰብ ረገድ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤን የሚቀይሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሸማቹን ፍላጎት ማርካት የሚችሉ ምርቶች ማቅረባቸውን የሚናገሩት ደግሞ በኤግዚቢሽኑ የሁለገብ አካል ጉዳተኞች ማቋቋሚያ ማህበር ምርቶችን ይዘው የቀረቡት አቶ ለማ ረጋሳ ናቸው፡፡

ከተፈጥሮ ምርቶች የተዘጋጁ ምንጣፍና የቤት ቁሳቁሶቻቸውን ይዘው መቅረባቸውን ገልጸው፤ ኤግዚቢሽኑ አምራቹ ምርቱምን እንዲያስተዋውቅ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

በኤግዚቢሽኑ የባህል አልባሳትን ይዛ መቅረቧን የገለጸችው ክርስቲና መኮንንም ለሸማቹ በዋጋና በጥራት ተመራጭ ምርቶችን ከማቅረቧም በላይ ኤግዚብሽኑ የገበያ ትስስርን በመፍጠር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግራለች፡፡