ሚኒስቴሩ፣ የተቋሙ ሰራተኞችና ተቋራጮች ለህልውና ዘመቻውና ለተፈናቀሉ ወገኖች የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ፣ የተቋሙ ሰራተኞችና ተቋራጮች ለህልውና ዘመቻውና ለተፈናቀሉ ወገኖች የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

ባህርዳር ታህሳስ 8/2014 (ኢዜአ) የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የአማራ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞችና ተቋራጮች ለህልውና ዘመቻውና ለተፈናቀሉ ወገኖች በጥሬ ገንዘብና በአይነት የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በርክክብ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ህወሓት በክልሉ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ያደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት የአሸባሪነቱን ጥግ የሚያረጋግጥ ነው።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ የሆነው አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ግብ ይዞ ቢንቀሳቀስም እኩይ ስራው በጥምር ጦሩ ተጋድሎ መክሸፉን ገልጸዋል።
መላው ህዝብ የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ፣ ለጥምር ጦሩ ስንቅ በማቅረብ፣ የወደሙ ሀብቶችን በመተካት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠናክር መሆኑን አመልክተዋል።
"ኢትዮ ቴሌ ኮም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የውሃ አገልግሎት መስሪያ ቤቶች በጥምር የወገን ጦር ነጻ በወጡ አካባቢዎች የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ፈጥኖ በመጠገን ለህዝቡ አገልግሎት ማብቃታቸው ይበል የሚያሰኝ ነው" ብለዋል።
ርእሰ መስተዳደሩ ተቋማቱና ሰራተኞቹ መሰረተ ልማቶችን ከመጠገን በተጨማሪ ላደረጉት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አብርሃም አዱኛ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን ለአገልግሎት እያበቃ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅ ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ ለተፈናቀሉ ወገኖች ተከታታይ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሚንስቴሩና ተጠሪ ተቋማት 5 ሚሊየን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
አሸባሪው ህወሓትና ግብረ አበሮቹን በግንባር ላይ ለሚፋለሙ የጸጥታ አካላትና ለተፈናቃይ ወገኖች ተከታታይ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰሎሞን ጣሰው ናቸው።
በህልውና ዘመቻው እየተሳተፉ ላሉ የጸጥታ ሃይሎች ከአገልግሎቱ ሰራተኞች በጥሬ ገንዘብ የተበረከተ የ6 ሚሊየን ብር ድጋፍ በቼክ አስረክበዋል።
በተጨማሪም ከተቋሙ ጋር የሚሰሩ ተቋሯጮች ያደረጉትን የ4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበርክተዋል።