ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉልን ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ መጥተናል

144

ታህሳስ 8/2014/ኢዜአ/ "ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው ለግል ወይም ለቤተሰብ ጉዳይ ሳይሆን የአገራችንን ጥሪ ተቀብለን ነው" ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዳያስፖራዎች ተናገሩ፡፡

በካናዳ ኦቶዋ የሚኖሩት የህክምና ባለሙያዋ አስቴር በላይነህ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ወዳጆቿ ያደረጉትን ጥሪ ተቀብለው ነው።

እርሳቸው ወደ አገር ቤት የመጡትም ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት እየተፋለመ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት መድሃኒቶችን ይዘው ነው።

"አሁን ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ለግል ወይም ለቤተሰብ ጉዳይ ሳይሆን የኢትዮጵያን ጥሪ ተቀብዬ ነው" ብለዋል።

አገራችን ለተፈጠረባት ወቅታዊ ችግር መፍትሄ መሻት፣ መተባበርና መተጋገዝ የሁላችንም ኃላፊነት በመሆኑ በውጭም በአገር ቤትም የምንገኝ ልጆቿ በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡልን ጥሪ መሰረት ወደ አገር ቤት የገባነውም ለግል ወይም ለቤተሰብ ጉዳይ ሳይሆን ለአገር ጥሪ ምላሽ ለመስጠት በመሆኑ የመጣንበትን ዓላማ ለማሳካት መዘጋጀት አለብን ነው ያሉት።

ከካናዳ ካግላሪ የመጡት ሌላኛው የህክምና ባለሙያ መላኩ ፍስሃ፤ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በተመሳሳይ ለሰራዊቱ የህክምና አገልግሎት የሚሆኑ መድሃኒቶችን ይዘው ነው።

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ይመራ በነበረበት ወቅት በነበረው አምባገነናዊ ስርዓት ተማረው ከአገር እንደወጡ ይናገራሉ።

በመሆኑም አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት በህዝብ ትግል ከስልጣን የተባረረውን አሸባሪ ቡድን ዳግም ወደ ስልጣን ለመመለስ የሚያደርጉትን ሴራ አጥብቀው እንደሚቃወሙ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ ዘብ ለሆነው የመከላከያ ሰራዊት በሙያ እገዛ  ከማድረግ ጀምሮ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ዲያስፖራው ወደ ሀገሩ ሲመጣ ለሀገር ጠቀሜታ ያላቸውን ነገሮች ይዞ በመምጣት አልኝታነቱን በተግባር ማሳየት እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ ከውጭ ይዘው የሚመጡትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ብቻ መመንዘር እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም