የኢትዮጵያ ቴሌኮም ሰራተኞች ማህበር ለመከላከያ ሰራዊት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

68

ታህሳስ 8/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ቴሌኮም ሰራተኞች ማህበር ለመከላከያ ሰራዊት የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።

በተመሳሳይ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች አገልግሎት የሚሰጠው ማህበር 300 ሺህ ብር የሚጠጋ የአይነት ድጋፍ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ቴሌኮም ሰራተኞች ማህበር ስብሳቢ አቶ ካሳሁን ሰበቃ ኀብረተሰቡ ለሰራዊቱ የሚያደርገው ድጋፍ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።

የማህበሩ አበላት ከዚህ ቀደም ለሰራዊቱ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ማካሄዳቸውን አስታውሰው፤ በዛሬው እለት ደግሞ ማህበሩ ለሰራዊቱ ያለውን አጋርነት ለመግለጽ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ነው የገለጹት፡፡

ማህበሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ  የግል ህብረት ስራ ማህበር በገንዘብ 289 ሺህ ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ  አድርጓል።

የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን አበራ በበኩላቸው ህይወቱን ለሀገሩ ክብር አሳልፎ ለሚሰጠው የመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረግ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኀብረተሰቡ ለሰራዊቱ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስቴር የፋይናስ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ዘላለም ፈተና ኀብረተሰቡ የሚያደርገው ድጋፍ   ለሰራዊቱ የሞራል ስንቅ ሆኖታል ነው ያሉት።

የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ በማስቀጠል ህዝቡ ለሀገርና ለወገን ክብር ለሚዋደቀው ለመከላከያ ሰራዊት አለኝታ መሆኑን በተግባር ማሳየት እንደሚገባውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም