በአፋር ክልል ለወደሙ ፖሊስ ጣቢያዎች መልሶ ማቋቋሚያ የ5 ሚሊየን ብር የቢሮ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

78

ታህሳስ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል በአፋር ክልል ላወደማቸው ፖሊስ ጣቢያዎች መልሶ ማቋቋሚያ የ5 ሚሊየን ብር የቢሮ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉ የተደረገው በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና በኢትዮ-ቴሌኮም ትብብር ነው።

ድጋፉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ሰመራ ከተማ በመገኘት ለአፋር ክልል ፕሬዚዳንት አወል አርባ አስረክበዋል።

በዚህም በሽብርተኛው የህወሃት ወራሪ ኃይል ውድመት የደረሰባቸውን የፖሊስ ጣቢያዎች መልሶ ለማቋቋም የሚያግዙ ኮምፒዩተር፣ ፕሪንተር፣ ጠረጴዛ፣ ወንበር እና መሰል የቢሮ መገልገያ ቁሶች ተበርክተዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጄኔራሉ ደመላሽ ገብረሚካኤል አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል በአፋርና አማራ ክልሎች ውድመት ያደረሰባቸውን የፖሊስ ጣቢያዎች መልስ በማቋቋም ወደስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ተከትሎ አሸባሪው ኃይል በአፋር ክልል ውድመት ያደረሰባቸውን ፖሊስ ጣቢያዎች መልሶ ለማቋቋም ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ ፖሊስና ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ እንደ ኮምፒዩተር፣ ፕሪንተርና ሌሎች የቁሳቁስ አይነቶች ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ድጋፉ አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ዘረፋና ውድመት የፈጸመባቸውን የፖሊስ ተቋማት መልሶ ለማቋቋም መነሻ እንደሚሆኑ አመላክተዋል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ፥ ኩባንያው እያከናወነ ከሚገኘው የቴሌኮም መሰረተ ልማት ግንባታ ጎን ለጎን በሽብርተኛው ወራሪ ኃይል ውድመት ለደረሰባቸው ተቋማት መልሶ ግንባታ የሚውል ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት ሃጂ አወል አርባ፤ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ጠላት የሆነው አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያን ልክ እንዲያውቅ ተደርጎ የተመታበት ድል ተመዝግቦ ከአፋር ምድር ጠራርጎ መውጣቱን አስታውሰዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም